ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 6/2016 (ኢዜአ)፦ የፌዴራል እና የክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች "ሃብት መፍጠር እና ማስተዳደር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኙ።

የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ''ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። 

በስልጠናው ላይ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን በዛሬው እለትም በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎበኝተዋል።

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎቹ ስልጠናው ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው በጉብኝታቸውም የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች መጠቀምና በአግባቡ የማስተዳደር ሂደቶችን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍፁም አሰፋ፤ በሁሉም መስክ ያሉ የኢትዮጵያ እምቅ ሃብቶችን በአግባቡ ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሃላፊዎቹ ሀብቶቹን በጋራ አልምቶ መጠቀምና በተገቢው መንገድ ማስተዳደር እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በጉብኝታቸው ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ በርካታ የልማት ክንውኖች መኖራቸውን እንዳዩ ጠቅሰው የሀገሪቷን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አመራሩን ጨምሮ የህዝቡ ትብብርና የጋራ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፋብሪካዎች የተመለከትናቸው ሀብት የመፍጠርና የማስተዳደር ልምድ እንዲሁም እንደ ሀገር ሀብቶችን በአግባቡ ማወቅ፣ መጠቀም እና ማስተዳደር የሚቻልበትን ሁኔታ ነው ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ገብረመስቀል ጫላ እና የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው በስልጠናውና በጉብኝቱ የመንግስትን የልማት ፖሊሲዎች በአግባቡ በመተግበር ሀገርን ወደ ተሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑንም ተገንዝበናል ብለዋል።

"ከዕዳ ወደ ምንዳ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተሰጠ ባለው ስልጠናም ኢትዮጵያ ጸጋዎቿን በመጠቀም ለቀጣዩ ትውልድ ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ለማስተላለፍ አመራሩ ሌት ተቀን መስራት እንዳለበት የጋራ አቋም የወሰድንበት ነው ያሉት።

ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በአግባቡ ተገንዝቦ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ለአገር እድገትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት በጋራ የሚያነሳሳ ስልጠና መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከፍተኛ አመራሮችም፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የመልማት አቅም ያላት በመሆኑ በየአካባቢው ያሉ እምቅ ሃብቶችን በማልማት ወደ ሀገራዊ ሃብት መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ፤ የብልጽግና ፓርቲ ለህዝቡ የገባውን ቃል ማስፈፀም የሚያስችል የአመራር አቅም የመፍጠርና ዓላማን የሰነቀ ስልጠና መሆኑን መግለፃቸው ይተወሳል።

ፓርቲው ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋጥ በሚያደርገው ጥረት በተለይም የአመራሩ የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በየደረጃው ያሉ አመራሮችን በስልጠና አቅም የመገንባት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም