አማራጭ ወደብ - የሎጅስቲክስ ዘርፍ ማነቆዎች ማቃለያ አማራጭ - ኢዜአ አማርኛ
አማራጭ ወደብ - የሎጅስቲክስ ዘርፍ ማነቆዎች ማቃለያ አማራጭ
አማራጭ ወደብ - የሎጅስቲክስ ዘርፍ ማነቆዎች ማቃለያ አማራጭ
በሰለሞን ተሰራ
የሎጂስቲክስ ምንነት
‘ሎጂስቲክስ’ የሚለው ቃል የመጣው "ሎጎስ" ከሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም ረጅም መንገድ ማለት ነው። ሎጂስቲክስ በጥቅሉ ሲታይ የንግዱ ዓለም ኩባንያዎች የምርት አቅርቦት ሰንሰለት በትክክለኛው ጊዜ፣ መጠንና ቦታ ሂደቱን የማሳለጥ እንዲሁም ገበያና ገበያተኛን የማስተሳሰር ፅንሠ ሃሳብ ነው። የአንድን ምርትና አገልግሎት ከመነሻ እስከ መድረሻ ያለውን ውስብስብ ዑደት የሚያጠቃልል ሲሆን ንግድን አፋጥኖ እና አቀላጥፎ የማሳለጥና ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነም ይገለጻል። ሎጂስቲክስ ከምርት እስከ ስርጭት ሂደትን ያቀፈ ሲሆን ከትራንስፖርት (መጓጓዝ) ጋርም ቁርኝት አለው። ከአገር የወጪና ገቢ ምርቶች ፍሰትና መጓጓዝ ጋር የተሳሰረው ሎጂስቲክስ የአቅርቦት ሰንሰለት ፍጥነት፣ የምርትና ዕቃዎች ተገኝነትን፣ የአቅርቦት ዋስትና እና ሂደቶች አቅፎ ይዟል።
አገራት በዓለም አቀፍ ንግድ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን የሎጂስቲክስ አቅማቸው አይተኬ ሚና ይጫወታል። አገራትም ከግል ዘርፉ ይልቅ በብዛት በሎጂስቲክስ ዘርፉ የልማት ድርጅቶችን መስርተው በኃላፊነት የሚንቀሳቀሱትም ለዚህ ይመስላል። አያሌ ተዋናዮች ያሉበት ይህ ዘርፍ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ታግዞ ለምርት ደህንነት መጠበቅና በተፈለገው ጊዜና ቦታ እንዲደርስ ለማድረግ ያስችላል።
በሎጂስቲክስ እሴት ሰንሰለት ውስጥ የተዋዋዮች (ደንበኛና አገልግሎት ሰጭ) ውል፣ የምርት ምንጭና መጋዘን ቆይታ፣ የትራንስፖርት፣ የወደብ፣ የጉምሩክ፣ የዕቃዎች ክትትልና አተገባበር ተጠቃሽ አንኳር ጉዳዮች ናቸው።
ሎጂስቲክስ ደንበኞች ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎት አሰጣጥን ታሳቢ ያደረጉ የራሱ የአፈጻጸም መለኪያዎች አሉት። በዚህም የአገራት የሎጂስቲክስ ስርዓት በዓለም አቀፍ መለኪያዎች ተመዝኖ የአፈጻጸም ደረጃው ደካማነትና ጠንካራነት ይቀመጣል።
የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ መልኮች
የአንድን አገር ማህበረ ኢኮኖሚ ችግሮች ለመቅረፍ ብቁ እና ውጤታማ ሎጂስቲክስ ስርዓት መገንባት ያሻል። የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ቀልጣፋና ውጤታማ ሎጂስቲክስ ወሳኝ ነው።
የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ አፈጻጸሟ ዝቅተኛ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ናት። የሎጂስቲክስ ስርዓቷ ደካማ የአመራር ስርዓት ያለው፣ ቅንጅታዊ አሰራር የሚጎድለው፣ በሎጂስቲክስ መሰረተ ልማትና የማጓጓዝ አቅም ረገድ ደካማ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። ለአብነትም ከቀዳሚ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች መካከል ከጊዜና ወጪ አንጻር ሲመዘን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ከባሕር ወደብ አለመኖር ጋር ተዳምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን እና አገራዊ ምጣኔ ሀብታዊ እምርታ ለማምጣት የራሱ አሉታዊ ተግዳሮት እንደሚያሳድር እሙን ነው።
ከትራንዚት ጊዜ፣ ከመርከቦችና የዕቃዎች ወደብ ላይ ቆይታ እንዲሁም ጭነት ከማንሳት አቅምና መሰል የአፈጻጸም መለኪያዎች አኳያ ብዙ የቤት ስራ መኖሩን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ያደረገው ሲሆን ከዚህም ባሻገር ከአቅራቢዎች፣ የመርከብ ባለቤቶችና ሌሎች የንግድ አጋሮች ጋር በሚኖረው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ኢትዮጵያ ከሕዝብ ብዛት ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ፈጣንና ግዙፍ ኢኮኖሚ ቢኖራትም የወጪና ገቢ ንግዷ በዋናነት በጅቡቲ ወደብ በኩል ይከናወናል፤ ይህም እያደገ ከመጣው የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ፍላጎት አንጻር ትልቅ ማነቆ ሆኗል።
በጥቅሉ የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስስ ዘርፍ በሚፈለገው ደረጃ ያላደገ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ውጤታማነት ያነሰ በመሆኑ የሎጂስቲክስ ስርዓቱን ማዘመን ይጠይቃል።
ሎጂስቲክስን ማዘመን
የዓለማችን ሉላዊነት የአገራትን ብርቱ ውድድር አንሮታል። በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተደራሽ የሆነ ምርትና አገልግሎት ለመስጠት የሎጂስቲክስ ዘርፉን ማዘመን አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ስርዓቷን ለማዘመን በጥልቅ ጥናት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂክ ሰነድ አዘጋጅታለች። ይህም የተጠናከረ ሎጂስቲክስ ዕሴት ሰንሰለት በመዘርጋት ከመነሻው እስከ መድረሻ ያለውን የዕቃዎችን የማጓጓዝ ፍሰት በማቀላጠፍ ደንበኞች ምርታቸውን በቀላሉ እንዲከታተሉ ያስችላል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የሎጂስቲክስ ዘርፉን መለካት ካልተቻለ መቆጣጠር አይቻልም። መቆጣጠር ካልተቻለ ደግሞ ማስተዳደር አዳጋች ይሆናል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ስለሌላት 90 በመቶ የሚሆነውን የንግድ እንቅስቃሴዋን በየብስ ትራንስፖርት ታከናውናለች። የኢትዮጵያ የሎጂስቲክስና ትራንስፖርት አገልግሎት ውጤታማነቱ በቂ ተርሚናል አገልግሎት የሌለው ነው።
የዕቃዎች የወደብ ላይ ቆይታ ጊዜ መራዘም አንዱ ቁልፍ ችግር ነው። መርከቦች ጭነታቸውን ሳያራግፉ ባሕር ላይ ይቆያሉ። ይህ ደግሞ ከሎጂስቲክስ ጊዜና ወጪ አኳያ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ አለው።
በ2010 ዓ.ም የታተመው ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂክ ሰነድ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ የገቢ ዕቃዎች ዓመታዊ መጠን ከ15 ሚሊዮን ቶን በላይ ደርሷል፡፡ በመንግስት አስመጪዎች ብቻ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ደረቅ ብትን ጭነት (የአፈር ማዳበሪያ፣ እህል፣ ከሰልና ስኳር) በዓመት በአማካይ ከ4 እስከ 8 ሚሊዮን ቶን ይገመታል። በወቅቱ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለጭነት ትራንስፖርት ብቻ (የባሕር፣ የወደብ አገልግሎትና የመንገድ) በዓመት በአማካይ 8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ይደረጋል፡፡
የሎጂስቲክስ ወጪ እና ብክነት እየጨመረ በመምጣቱ አላሰፈላጊ ወጪና የሀብት ብክነት መቀነስ ግድ ይላል። የሎጂስቲክስ ወጪ በአማካይ የአንድን አገር ጂዲፒ (የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት) ከ14 በመቶ እስከ 35 በመቶ የሚሸፍን ነው። የኢትዮጵያ ወጪ ግን ከዚህም የላቀ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የሎጂስቲክስ ስርዓቱን ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መምራት ባለመቻሉ እንደሆነ ይገለጻል። በዚህም ለትራንስፖርት፣ ለወደብና የመጋዘን ኪራይ፣ ለኮንቴይነር፣ ለግብይትና ሽያጭ፣ ለተለያዩ እቃዎችና ምርቶች እንዲሁም ለሌሎች የሎጅስቲክስ ወጪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣለች።
ይህ በየጊዜው እየናረ የመጣው የሎጂስቲክስ ዋጋ ዓለም አቀፍ የንግድ ተዋናዮችን ወጪ በመጨመር በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትታቸው እንዲቀንስ ያደርጋል። የአገር እድገትንም ወደ ኋላ ይጎትታል።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በሎጂስቲክስ ሰንሰለት የሚደረጉ ወጪዎች በምርቶች የመጨረሻ ዋጋ ላይ ከ20 እስከ 27 በመቶ ጭማሪ እንዲደረግ ምክንያት ይሆናሉ። በኢትዮጵያም የዕቃዎች የማጓጓዝ እና የጭነት ወጪ ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነጻጸር የ60 በመቶ ብልጫ አለው።
አማራጭ ወደቦችን ማማተር
ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ 44 ሀገራት ወደብ የላቸውም። እነዚህ አገራት እንደየነባራዊ ሁኔታቸው የሎጂስቲክስ ስርዓት ዘርግተው ይንቀሳቀሳሉ። በተለይም የተሸጋጋሪ (የትራንዚት) ትራንስፖርት ስርዓት ዋንኛው አማራጭ አድርገው ይጠቀማሉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ካላቸው ጎረቤት አገራት ጋር የትራንዚት ትራንስፖርት ስርዓት ዘርግታ ትገለገላለች። ባቡርን ጨምሮ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሰረተ-ልማቶች ግንባታ አድርጋለች። ከጎረቤት አገራት ጋር የብዝሃ ወደብ አጠቃቀም ስምምነቶች ለማድረግም ጥሩ ትስስር እየፈጠረች ነው።
የኢትዮጰያ የወጪና ገቢ ንግድ እንቅስቃሴ ወጪ መናር አማራጭ ወደቦችን መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም የሎጂስቲክስ ስርዓቷን የማዘመንና የማሻሻል ግቧን ለማሳካት ያግዛል። በተለይም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የንግድ ዕቃዎች መተላለፊያ ኮሪደሮችን በማስተሳሰር በኢኮኖሚ መስክ እምርታ ለማምጣት ያግዛሉ።
የአማራጭ ወደቦች መኖር የባሕር ትራንስፖርትና ብዝሃ (Multimodal) የትራንስፖርት አገልግሎትን በማዘመን የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማሳጠር፣ የጊዜና ሀብት ብክነትን ለመቀነስ ያግዛል። በኢኮኖሚ ኮሪደሮች እና በአማራጭ የባሕር ወደቦች የሚደረግ ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ በመጠንና በአይነት ለማሳለጥ ዋነኛው አማራጭ ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
በውስን ወደቦች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን ከአገራት ጋር በሚደረጉ የንግድ ስምምነቶች ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ከማገዝ ባለፈ የመደራደር አቅሟንም ይጨምራል። ይህም የአገሪቱን ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሁነኛ ሚና ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ በጅቡቲ ወደብ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይህ ደግሞ እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት በቅጡ ለማስተናገድ አዳጋች ሆኗል።
ስለሆነም የቀጣናው አገራትን ወደቦች በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የማልማትና የመጠቀም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ደንጌ ቦሩ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚሸከም የተቀላጠፈ የወጪና ገቢ ንግድ ሎጂስቲክስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም የሚያስችሉ ስራዎች እየከናወነች መሆኑንና ኢትዮጵያን የቀጣናው ሎጂስቲክስ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አማራጭ ወደቦች የጅቡቲ ወደብን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ እና ወጪንም ለማቃለል ዕድል ይፈጥራል። ከአማራጭ ወደቦችን መካከል የላሙ፣ ሞምባሳ እና በርበራ ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያ አማራጭ ወደቦች መጠቀሟ ከኬንያና ደቡብ ሱዳን ጋር በትራንስፖርት የሚያስተሳስረው 'ላፕሴት' ለተሰኘው ፕሮጀክት መሳለጥ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ብልፅግናዋን ለማረጋገጥና እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚ ለማስተናገድ የሎጂስቲክስ ስርዓትን ማዘመንና ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን አቶ ደንጌ ቦሩ ገልጸው ነበር። የብዝሀ ወደብ አጠቃቀም ለማስፋትም ቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
በጎረቤት አገራት በኩል የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች ሲጠናቀቁ በጋራ የመበልፀግ፣ አፍሪካን ለማስተሳሰር እንዲሁም ለኢትዮጵያ ትልቅ የገበያ ዕድል ለመፍጠር ሁነኛ ፋይዳ እንዳላቸውም ነው ያነሱት። የባቡርና የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ በላፕሴት ሰባት ፕሮጀክቶች አሉ። ኢትዮጵያ እስከ ሞያሌ ያለውን ፈጣን መንገድ ጨምሮ የበኩሏን ሃላፊነት ፈጽማለች።
የላፕሴት ፕሮጀክት አማራጭ የወደብ አጠቃቀም ከማሳለጥ በተጨማሪ አፍሪካን እርስ በርስ በንግድ ለማስተሳሰር ግብ ይዞ ወደ ትግበራ ለገባው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስኬት ጉልህ ሚና አለው። የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያን ጨምሮ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማትን በመዘርጋት ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማዕከል እንድትሆን እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
የሎጂስቲክስ አስተላላፊዎች
የሎጂስቲክ ዘርፍ በርካታ ተዋናዮችንና ተቋማትን ያካተተ ሲሆን የባሕር፣ የየብስና የአየር ትራንስፖርት፣ ወደቦች፣ ጉምሩኮች፣ የፋይናንስ እና የንግዱ ዘርፍ ተቋማትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ አስተላላፊዎች ዘርፉን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች እንደተጀመሩ ይነሳል። ነገር ግን ከመሰረተ ልማት፣ ዓለም አቀፍ የማጓጓዝ ልምድ፣ የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነት፣ የዕቃዎች ክትትልና ቁጥጥር እና በጊዜ ውጤታማነት ሲመዘኑ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች ያላቸው ዓለም አቀፍ ልምድ በቂ የሚባል አይደለም።
መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ሪፎርሞች እያካሄደ ይገኛል። ከሪፎርም ስራዎች መካከል የግል ባለሀብቶች በሎጂስቲክስ ዘርፉ በስፋት ማሳተፍ፣ ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉና ተወዳዳሪነትን የሚጨምሩ ዓለም አቀፍ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ።
የሎጅስቲክስ ዘርፉን ለማዘመን መፍትሄ ተብው ከተቀመጡ አማራጮች መካከል የውጭ አገር አገልግሎት ሰጪዎች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር 49 በመቶ ድርሻ በመግዛት በጭነትና አስተላላፊነት ዘርፍ በጥምረት እንዲሰሩ ፈቃድ መስጠት የሚለው በጉልህ ይጠቀሳል።
ይህም ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊ አስተዳደር ያለው የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠትና የእውቀት ሽግግር ለማምጣት ይረዳል።
ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን በመጠቀም የጉምሩክ ክሊራንስ መሰረተ ልማቶችን መገንባት እና የማስፋፊያ ስራዎችን ማከናወን ቀጣዩ የቤት ስራ ይሆናል።
በሀገራችን የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች፣ የችግሮቹ መገለጫዎች፣ የችግሮቹ መንስኤዎችና እያስከተሉት ያለው ጉዳት ከሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ጋር በቀጥታ የሚቆራኙ መሆኑ እሙን ነው።
በመሆኑም የበርካታ ጉዳዮች ስብስብና ትስስር የሆነውን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በሁለንተናዊ መልኩ ማዘመን ያስፈልጋል።
በሎጂስቲክስ ሥርዓቱ ውስጥ ዘርፉ የሚመራበት ህግና ፖሊሲ፣ የተዘረጋው መሠረተ ልማት፣ ዘርፉን የሚመሩና የሚቆጣጠሩ ተቋማት አሠራር፣ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የሎጅስቲክስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብቃት፣ ዓቅምና መሰል ሁኔታዎች በልዩ ትኩረት ሊታዩና ሊሰራባቸው ይገባል።
ይህን ማሳካት ሲቻልና አማራጭ ወደቦችን የማማተር ጉዳይ ሲታከልበት ፈጣን ልማትን ማረጋገጥና ከልማቱም ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ አገራዊ ግቦችን ዕውን ማድረግ ይቻላል፡፡