ቀጥታ፡

የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ተመዘገበ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 6/2016 (ኢዜአ)፦ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ ዕውቅና በማግኘት ተመዘገበ፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በሣውዲ አረቢያ ሪያድ በተካሄደው 45ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና ባህል ድርጅት የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፤ የጌዴኦ ህዝብ በጥምር ግብርና ሥራዎች የዕጽዋዕት፣ የፍራፍሬ፣ የሰብል ምርቶችና በጣዕሙ የሚታወቀውን የይርጋጨፌ ቡና በማምረት እንደሚታወቅ አብራርተዋል።

ህብረተሰቡ ሀገር በቀል ዕውቀት ተጠቅሞ የአየር ሚዛን የተስተካከለ እንዲሆን በማስቻል እንዲሁም የመሬት አጠባበቅ እና አያያዝ ልምዱ ለሌሎች ህዝቦች ልዩ ተሞክሮና ልምድ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ቀልብን ከሚስቡ የቱሪዝም ኃብቶች መካከል የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በእጅጉ አስደማሚ መሆኑንም ገልጸዋል።

መልክዓ ምድሩን ሳቢ ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል በምስራቅ አፍሪካ ረዥም እድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት የትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ መያዙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መልክዓ ምድሩ በውስጡ ከ6 ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮችን የያዘ ሲሆን፤ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች፣ ለውጭና አገር ውስጥ ጎብኚዎች ቀልብን የሚስቡ ገጽታዎችን የተላበሰ ነው።

ከትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶች መካከል ቱቲፈላ፣ ጨልባ ቱቲቲ፣ የሴዴ ትክል ድንጋይ መካነ ቅርሶች በተጨማሪ የድንጋይ ላይ ጽሑፍን የያዘ መሆኑ ይታወቃል።

በትውልድ ቅብብሎሽ ሲጠብቀው የቆየ ጥብቅ ደን የያዘ ሲሆን፤ ጥምር ግብርናም የሚካሄድበት መሆኑ ሌላው ልዩ የሚያደርገው ገጽታው እንደሆነም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

የጌዴኦ መልክዓ ምድር ቅርስ የማኅበረሰቡን መስተጋብር፣ አኗኗር ከማሳየቱም ባለፈ የበርካታ አእዋፋት፣ እንስሳትና አዝርዕት መገኛ ሲሆን ሰው ከተፈጥሮ ጋር እንዴት መኖር እንደሚችል የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ቅርሱን በዓለም ወካይ ቅርስነት ለማስመዝገብ ከ2005 ዓ. ም. ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቶ በዛሬው እለት በሪያድ በተካሄደው 45ኛው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።

ዩኔስኮ አንድን ቅርስ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከሚያስችላቸው ጉዳዮች መካከል የቅርስ ጥበቃ አዋጅ አንዱ በመሆኑ በቅርሱ አጠባበቅ ላይ የሕዝቡን፣ የባለድርሻ አካላት እና የቅርስ ጥበቃ ኮሚቴዎችን ሚና በዝርዝር የያዘ አዋጅ መዘጋጀቱ ይታወሳል።

መልክዓ ምድሩ የሚገኝበት ካርታ መዘጋጀቱና ሃብቱን የበለጠ ለመጠበቅ የሚረዳ አጥር እንዲኖረው መደረጉንም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።

ቅርሱ እንዴት ይጎበኛል? ከማን ምን ይጠበቃል? የአስተዳደር ጉዳዮች እንዴት ይከወናሉ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ የአምስት ዓመት የቱሪዝም ልማት ዕቅድ ሰነድ በማዘጋጀት ለዩኔስኮ ተልኮ ዕቅዱ በዩኔስኮ ባለሙያዎች ተገምግሞ ተቀባይነት ማግኘቱ ቀደም ብሎ መገለጹ አይዘነጋም።

የጌዴኦ መልክዓ ምድር በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ ለቅርሱ ዘላቂ እንክብካቤ እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ ትልቅ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን እንደሚያስችለው አባላቱ ተናግረዋል።

አንድን ቅርስ በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ በራሱ ግብ ባለመሆኑ ከሃብቱ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት ሕብረተሰቡ እንክብካቤ እና ድጋፉን ሊያጠናክር እንደሚገባ አባላቱ አሳስበዋል።

ቅርሱን በተመለከተ ጥያቄና ማብራሪያ የሰጡት የኮሚቴው አባል አገራት በቀጣይ ሃብቱን የበለጠ ለመጠበቅ የሚያስችሉ እርምጃዎችን በፍጥነት እንዲተገበሩ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡

የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ ለቀረቡት ማብራሪያዎችና ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

መንግስት ቅርሱን ለመጠበቅ ከክልሉ መንግስትና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

የዩኔስኮ የዓለም ቅርሶች ኮሚቴ 21 አባል ሀገራት ያሉት ሲሆን ከአፍሪካ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ ተካተውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም