ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገርን ሉዓላዊ አንድነት ማጽናት በሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል - ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገርን ሉዓላዊ አንድነት ማጽናት በሚያስችል አስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝ በመከላከያ ሰራዊት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ ገለጹ።

በአገር መከላከያ ሠራዊት ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ በ12ኛ ዙር አጭር ኮርስ ያሰለጠናቸውን የመገናኛ አመራሮች አስመርቋል።

በዚሁ ወቅት በመከላከያ ሠራዊት የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ሜጀር ጀነራል ከፍያለው አምዴ፣ ሰራዊቱ የተሰጠውን አገራዊና ህዝባዊ ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።

የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን በማክሸፍና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የአገርን ሉዓላዊ አንድነት እየጠበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት እራሱን በሰው ሃይል እና በዘመናዊ ትጥቅ በማደራጀት የአገርን ሉዓላዊ አንድነትን ለማጽናት በአስተማማኝ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ብቁ የመገናኛ ኢንፎርሜሽን አመራርና ሙያተኛን በማፍራትና ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ መሸከም የሚችል አቅም በመፍጠር የውጊያ ድጋፍና አጠቃቀምን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እየተቻለ ነው ብለዋል።

የሰራዊቱን ግዳጅ የመወጣት አቅም ለማሳደግም ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች የተመለመሉ የመገናኛ ኢንፎርሜሽን አመራሮችን አቅም ማሳደግ የሚያስችል ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።

ተመራቂ የመገናኛ ኢንፎርሜሽን አመራሮች በውትድርና ህይወት ያካበቱት ልምድ እና የወሰዱት ስልጠና ግዳጅ የመፈጸም አቅማቸው እንዲጎለብት ማድረጉን ተናግረዋል።

የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ አዛዥ ኮሎኔል አራጋው መሃመድ፣ ኮሌጁ ሰራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ብቁ የመገናኛ አመራርና ሙያተኛ እያፈራ ነው ብለዋል።


 

ኮሌጁ የሰራዊቱን የመፈጸም አቅም ለማጎልበት የነበረውን የትምህርት ሥርዓት በማሻሻል ለ12ኛ ጊዜ ብቁ የአጭር ኮርስ የመገናኛ ኢንፎርሜሽን አመራሮችን ማስመረቁን ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹም የነበራቸውን ዕውቅት፣ ልምድና ክህሎት በማጎልበት ስራቸውን በእቅድ ላይ የተመሰረተ ማድረግ የሚያስችል ትምህርትና ስልጠና ሲከታተሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ዘሪሁን በቀለ በበኩላቸው ለምርቃት የበቁት የመገናኛ ኢንፎርሜሽን አመራሮች የአገርን አንድነት ማስጠበቅ የሚያስችል ስልጠና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።


 

በቆታቸውም ሰራዊቱ የሚከተለውን ሳይንሳዊ የውጊያ ጥበብ በማሻሻል ለአዛዦች ውሳኔ የሚረዳ ምክርና አስተያየት ማቅረብ የሚያስችል ሙያዊ ስልጠና አግኝተዋል ብለዋል።

የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ኮሌጅ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት "የመገናኛ ትምህርት ቤት" በሚል ሥያሜ በ1953 ዓ.ም ተመስርቶ በራዲዮ ጥገና፣ በማዞሪያ ስልክ ኦፕሬተር፣ በጄኔሬተር ኦፕሬተር፣ በሞርስ ኦፕሬተር፣ በቴሌፎን ኦፕሬተርና በታይፒስት ሥራ እንደጀመረ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም በኮሙኒኬሽንና ኤሌክትሮኒክስ፣ በኢንፎርሜሽንና ሴኪዩሪቲ እንዲሁም በማኔጅመንት ትምህርት ክፍሎች በዲግሪ፣ በዲፕሎማ፣ በመካከለኛ፣ በአጭር ኮርስ፣ በሰልጥኖ አሰልጣኝ፣ በሪፍሬሽመንት፣ ለሲቪሎች በድጋፍና በሰርተፊኬት ለውጭ ሰልጣኞች ትምህርትና ሥልጠና በመሥጠት በመከላከያ ሠራዊት ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ የሚመራ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም