ቀጥታ፡

የፌዴራል ፖሊስ የሪፎርም ስራዎች የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል ተቋማዊ አቅም እንዲፈጠር አድርገዋል - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 5/2016 (ኢዜአ) ፦ የፌዴራል ፖሊስ የሪፎርም ስራዎች የህዝብን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል ተቋማዊ አቅም እንዲፈጠር ማድረጋቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራልና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ2015 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራሮችና አባላት የእውቅናና ምስጋና መርኃ ግብር በአዲስ አበባ አካሂዷል።


 

በመርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

በዛሬው ዕለት እውቅና የተሰጣቸው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ሥር እንዲሁም በዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙ የሥራ ክፍሎችና ለኮሚሽነር ጄኔራል ተጠሪ የሆኑ መምሪያዎች መሆናቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የሪፎርም ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

የሪፎርም ስራዎቹ የፌዴራል ፖሊስ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በኩል ሰፋፊ ስራዎችን በብቃት የማከናወን አቅሙ እንዲጎለብት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ሀይሎች ሲያጋጥማት የነበረውን የጸጥታ ችግር ለመመከት ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን ገልጸዋል።

በ2015 ዓ.ም በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ እና በአቅም ግንባታ ረገድ ትላልቅ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል ተቋማዊ አቅም መገንባቱንም ተናግረዋል።

የኢንተለጀንስ አቅምን በማጠናከር በህገ-ወጥ የመሳሪያ ዝውውር እና የተደራጁ ወንጀሎችን መቆጣጠር መቻሉን ጠቁመዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ በጸረ ሰላም ሀይሎች ላይ ክትትል በማድረግ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ተደራጅተው የህዝብን ሰላም በሚነሱና የአገርን ልማት በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የአገርን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ፕሮፌሽናል የሆነ የፖሊስ አገልግሎት በመላ ኢትዮጵያ ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኜ እንዳሉት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የፌዴራል ፖሊስ ሰፊ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ አከናውኗል።

በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ተልዕኮውን መወጣት የሚያስችለው አቅም መፍጠሩን ገልጸው ጠቅላይ መምሪያው ባከናወነው የመፈጸም አቅምን የማሳደግ ሥራ የወንጀል መከላከል አድማስ እንዲሰፋ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች አገራት እንዲሁም አህጉራዊ የፖሊስ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ተቋሙ አሁን ላይ ልምድ የሚወሰድበት ተመራጭ ተቋም ሆኗል ብለዋል።

እውቅና ከተሰጣቸው የፌዴራል ፖሊስ አባላት መካከል ምክትል ኮማንደር ወርቅነሽ ዘውዴ እውቅናው ለበለጠ ስራ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ባልነበረ ሁኔታ ግብአቶች እየተሟሉ መሆናቸውን ገልጸው አመራሮች ለሰጡት ትኩረት ምስጋና አቅርበዋል።

ኢንስፔክተር አንድነት ሲሳይ በበኩላቸው እውቅናው ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጸው ቀን ከሌሊት በመስራት የሚጠበቅብንን የህዝብ አደራ ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራልና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል እውቅና ተሰጥቷቸዋል።


 

በተመሳሳይ ለአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የክብር አምባሳደርነት መታወቂያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም