ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ልማትን ማሳካት እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ማሳያ ነው--የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ልማትን ማሳካት እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ማሳያ ነው--የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ሆሳዕና፤መስከረም 5 /2016 (ኢዜአ)-ውስጣዊ አንድነትን አጠናክሮ ያሉትን ጸጋዎች ማልማት ከተቻለ ሀገራዊ የእድገት ጉዞን እውን ማድረግ እንደሚቻል የሕዳሴው ግድብ ማሳያ ነው ሲሉ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ግድቡ ድህነትን ለማሸነፍና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማሳካት አስተዋጾው የጎላ መሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትምህርት ክፍል መምህር ሙላለም ኃይለ ማርያም እንዳሉት፣ የሕዳሴው ግድብ በዘመናት መካከል ሲታቀድ ቢቆይም የአሁኑ ትውልድ ቆርጦ በመነሳቱ ሊገነባ ችሏል።
በተለይ በግድቡ ላይ ከጅማሮ ጀምሮ የነበረውን ጫና ተቋቁሞ ለማለፍ መንግስትና ህዝብ ያሳዩት ቁርጠኝነትና አንድነት ለስኬቱ ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።
"የሕዳሴው ግድብ አሁናዊ ገጽታው ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ያሉትን ፀጋዎች ማልማት ከተቻለ የተጀመረውን ሀገራዊ የእድገት ጉዞን እውን ማድረግ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው" ሲሉም መምህር ሙላለም ገልጸዋል።
በመሆኑም የውስጥ አንድነትንና ሰላምን በማጠናከር ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
እንደ መምህሩ ገለጻ፣ የግድቡ መጠናቀቅ ለኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት፣ ለቱሪዝም እና የሥራ ዕድል አማራጮችን ለማስፋት አይነተኛ ሚና ይጫወታል።
በሀገሪቱ ፈጣን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ አጋዥ በመሆኑም ዜጎች ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ አብሮ በማደግ መርህ ላይ እንደማትደራደር የገለጹት መምህር ሙላለም፣ የሕዳሴው ግድብ በቀጣይ በዲፕሎማሲ መስክ ለሚሰሩ ሥራዎች ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም አመልክተዋል።
ሌላው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ አበራ ሄቢሶ በበኩላቸው እንዳሉት የሕዳሴ ግድብ የእዚህ ትውልድ አሻራ ነው።
ግድቡ ለአራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት መድረሱ አንድነትና ህብረትን ማጠናከር ከተቻለ ጫናዎችን በመቋቋም ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
ተባብሮ መስራት እድገትን ለማፋጠንና ከድህነት ለመውጣት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ከግድቡ ስኬት ትምህርት መውሰድ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
ተባብሮ ለጋራ ዓላማ መስራት ያለውን ውጤት ከሕዳሴው ግድብ በመማር ሁሉም ዜጋ ለተጨማሪ የልማት ስኬት መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በመሆኑም ዜጎችና መንግስት አብሮነታቸውን በማጠናከር ያልተገቡ የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም ልማትን ማጠናከር አለባቸው ብለዋል ።
እንደ አቶ አበራ ገለጻ፣ የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቅ ግድቡ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደሌለው ተጨባጭ ማሳያ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቁን መንግስት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።