በአማራ ክልል የኮሌራ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የኮሌራ መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
ባህር ዳር፤ መስከረም 5 / 2016(ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሰዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የኮሌራ በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩ ተገለጸ።
የክትባት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ የክልልና የፌዴራል የዘርፍ አመራሮች በተገኙበት በባህር ዳር ዛሬ ተከናውኗል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የኮሌራ በሽታ ተከስቶ ሰዎችን ለህመም ዳርጓል።
ክስተቱም በ28 ወረዳዎች እንደነበር አስታውሰው፤ በተቀናጀ አግባብ በተከናወነው ስራ ወደ 11 ወረዳዎች ማውረድ መቻሉንና በሽታው ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በሽታውን ለመከላከል ምግብን አብስሎ መመገብ፣ የግልና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ አስፈላጊ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በተጓዳኝ ክትባት ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።
ከፌዴራል የጤና ተቋማትና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በመተባበር ባህር ዳርና ጎንደርን ጨምሮ በዘጠኝ ከተሞችና ወረዳዎች ክትባቱ ይሰጣል ብለዋል።
ክትባቱም ከመስከረም 5 እስከ 10 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥና ክትባቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልየህብረተሰቡ ሃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ፤ በክልሉ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ከአመራሩ እስከ ጤና ሙያተኛው በተቀናጀ አግባብ መከላከል በመቻሉ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ተደርጓል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው ክትባት በሽታውን የመከላከልና የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ጎን ለጎን ዓይነተኛ መፍትሄ በመሆኑ ህብረተሰቡ በየአካባቢው የክትባት ማዕከል በመሄድ ክትባቱን መውሰድ እንዳለበት አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር ከዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች ጋር በመሆን ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሌራ ክፍል መሪ አቶ ሻምበል ወርቁ ናቸው።
በሽታውን ለመከላከል የሚካሄደው ክትባት ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና በሽታውን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንዲቻል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በማስጀመርያ መርሃ-ግብሩ ላይ ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተጨማሪ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።