ሆስፒታሉ የፊስቱላ እና የማህፀን መንሸራተት ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ሆስፒታሉ የፊስቱላ እና የማህፀን መንሸራተት ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ
ነቀምት ፤ መስከረም 5/2016 (ኢዜአ) ፡- የነቀምቴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፊስቱላ እና የማህፀን መንሸራተት ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
ሆስፒታሉ አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩ ይፋ ሲደረግ እንደተገለጸው፣ ከእዚህ በፊት አገልግሎቱ እንደ ምዕራብ ኦሮሚያ በመቱ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ ነበር።
በአሁኑ ወቅት የነቀምቴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተጨማሪ ማዕከል ሆኖ በማገልገል ሕክምናውን ለመጀመሪያ ጊዜ መስጠት መጀመሩን የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢተፋ ሺፈራ ገልጸዋል።
ዶክተር ኢተፋ እንደገለጹት ሕክምናው እየተሰጠ ያለው ከዞን ጤና ጽህፈት ቤትና ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ነው።
"የቤተሰብ መሰረት የሆነችውን እናት ማከም ቤተሰብን እንደ ማከም ነው" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የፊስቱላ እና የማህፀን መንሸራተት ሕክምና አገልግሎት በሆስፒታሉ መሰጠት መጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ህክምናውን የሚፈልጉ ወገኖች በቅርበት ስለሚታከሙ ካልተገባ ወጪ የሚታደጋቸው ከመሆኑ በላይ በገጠማቸው የጤና እክል በቤት ውስጥ ተደብቀው ሲሰቃዩ የነበሩ እናቶች ወጥተው እንዲታከሙ ያደርጋል ብለዋል።
በሆስፒታሉ የሴቶች እና ህፃናት ሕክምና ባለሙያና የፊስቱላ እና የማህፀን መንሸራተት ህክምና ክፍል አስተባባሪ አቶ ጥሩነህ አስራት በበኩላቸው በተለይ በገጠራማው አካባቢ ያሉ ሴቶች በችግሩ ምክንያት ጤናቸው ሲቃወስ በፍራቻ ችግራቸውን ደብቀው በቤት ውስጥ ይሰቃዩ እንደነበር ገልፀዋል።
የሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች የሕክምና አገልግሎቱን የሚፈልጉ እነዚህን እናቶች ለማገዝ እየሰሩ መሆኑንም ዶክተር ኢተፋ አመልክተዋል።
"በሁለት ሳምንት የሕክምና አገልግሎት 15 እናቶች ከፊስቱላ እንዲሁም 11 እናቶችን ደግሞ ከማህጸን መንሸራተት የጤና ችግር እንዲያገግሙ ለማድረግ ተችሏል" ብለዋል።
ህክምናው ተጠቃሚ ከሆኑ እናቶች መካከል ወይዘሮ ዳሼ ወርቁ በማህፀን መንሸራተት ምክንያት ለአራት ዓመታት ሲሰቃዩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በቤት ውስጥ በባህላዊ መንገድ ሲወልዱ ለማህጸን መንሸራተት መጋለጣቸውን የገለጹት ወይዘሮ ዳሼ፣ በወቅቱ ከፍለው ለመታከም የገንዘብ ችግር ስላለባቸው በሽታቸውን ደብቀው ለመኖር መገደዳቸውን ተናግረዋል።
በማህፀን መንሸራተት ችግር ምክንያት ለአስር ዓመታት ሲሰቃዩ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ደሴ ጉተማ ናቸው።
በእዚህ የጤና ችግርም ረዥም መንገድ ለመሄድና እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣ በተለይ ህብረተሰቡ ለበሽታው ያለው አመለካከት ጥሩ አለመሆን ውስጣቸውን እንደጎዳው ገልጸዋል።
በእዚህም የጤና ችግራችውን በግልፅ አውጥቶ ለመናገር መቸገራቸውን ጠቁመው፣ "በአሁኑ ወቅት ህክምናውን በማግኘቴ እና ጤናዬ በመመለሱ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ጤና ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሲስተር ሽታዬ በቀለ በበኩላቸው በሆስፒታሉ እና "ዊንግስ ኦፍ ሄልፕ" በተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ድጋፍ ለ150 ሴቶች የህክምና አገልግሎቱ በነጻ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርም ለህክምና አገልግሎቱ የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ህክምናው በሆስፒታሉ መጀመሩ ለበርካታ እናቶች እረፍት የሚሰጥ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።