ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራሮችና አባላት እውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 5/2016 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በ2015 ዓ.ም የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራሮችና አባላት የእውቅናና ምስጋና መርኃ ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራልና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችና የክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ታድመዋል።

በዛሬው ዕለት እውቅና የተሰጣቸው በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ሥር እንዲሁም በዋና መሥሪያ ቤት የሚገኙ የሥራ ክፍሎችና ለኮሚሽነር ጄኔራል ተጠሪ የሆኑ መምሪያዎች መሆናቸው ተጠቁሟል። 


 

በመርኃ ግብሩ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራልና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በተመሳሳይ ለአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የክብር አምባሳደርነት መታወቂያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ ዳኜ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የፌዴራል ፖሊስ መጠነ ሰፊ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራ አከናውኗል። 

በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ተልዕኮውን መወጣት የሚያስችለው አቅም መፍጠሩን ገልጸው ጠቅላይ መምሪያው ባከናወነው የመፈጸም አቅምን የማሳደግ ሥራ የወንጀል መከላከል አድማስ እንዲሰፋ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች አገራት እንዲሁም አህጉራዊ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ተቋሙ አሁን ላይ ልምድ የሚወሰድበት ተመራጭ ተቋም መሆኑን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ነብዩ አመላክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም