ቀጥታ፡

የቡድን-77 አገራት ጉባዔ ዛሬ በሀቫና ይጀመራል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፡- የቡድን-77 አገራት ጉባኤ ዛሬ ሲጀመር በዋናነት ቁልፍ በሆኑ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚወያይ ተገለጸ።

የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ እንደገለጹት ሀቫና ለሁለት ቀናት በምታስተናግደው ጉባዔ ከ100 በላይ የሀገራት መሪዎችና ተወካዮችን ተቀብላለች።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክም በጉባዔው ለመታደም ዛሬ ጠዋት ሀቫና መግባቱ ይታወሳል።

የወቅቱ የቡድን-77 ፕሬዝዳንት የሆነችው ኩባ ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን ሰፊ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጉባዔው በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት እየጨመረ የመጣውን የብድር ማነቆ ለመፍታት በፋይናንስ ሥርዓት ማሻሻያ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ይመከራል ተብሏል።

በባለብዙ ወገን ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የተነገረለት ቡድን-77 ኩባ መዲና ሀቫና ውስጥ በሚያካሂደው ጉባዔው አዲስ ዓለም አቀፍ ምጣኔ ኃብታዊ ሥርዓት ለመገንባት አልሟል ።

ቡድኑ ባለፉት ዓመታት የአባል አገራቱን የጋራ ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም ማስተዋወቅ ላይ አልሞ ሲሰራ ቆይቷል።

ቡድን-77 እኤአ በ1964 ከጄኔቫ የመንግሥታቱ ድርጅት የንግድና ልማት ኮንፍረንስ በኋላ በ77 አዳጊ አገራት ተመስርቶ ስያሜውም ከዚሁ መውሰድ የቻለ ጥምረት ነው።

አሁን ላይ ቡድኑ 80 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ እንደሚወክል መረጃዎች ያሳያሉ።

በአሁኑ ጊዜ ቡድኑ 134 አገራትን በአባልነት ያካተተ ሲሆን ቻይና ሙሉ አባል ባትሆንም ልዩ ሚና እንዲኖራት ተደርጓል።

እኤአ በ2015 ቡድኑን የተቀላቀለችው ደቡብ ሱዳን ደግሞ የመጨረሻዋ አባል አገር ሆና ተመዝግባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም