የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የተጀመሩ ስራዎችን በሁሉም ክልሎች ለማስፋት በቅንጅት ይሰራል-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የተጀመሩ ስራዎችን በሁሉም ክልሎች ለማስፋት በቅንጅት ይሰራል-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የተጀመሩ ስራዎችን በሁሉም ክልሎች ለማስፋት በቅንጅት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፁ።
15ኛው የፌደራል፣ የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ እና ሀገራዊ ገለልተኛ የፖሊስ አማካሪ ምክርቤት ጉባኤ ተካሂዷል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል ጨምሮ የሁሉም ክልሎች እና የሁለት ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዝዳንት ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት፤ በጉኤው በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የተከናወኑ የጸጥታ ስራዎች መገምገማቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የፖሊስ አቅምን በማሳደግ ለቀጣይ ስራዎች ዝግጁ ማድረግ የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ አቅምን ማጎልበት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉም እንዲሁ፡፡
ለዚህ ደግሞ ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበር ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ በእቅዱ ላይ በመወያየት ሁሉም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የጋራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በ2015 ዓ.ም በሁሉም ክልሎች የተከናወነውን የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላትን መልሶ የማደራጀት ስራ አፈፃፀም ግምገማ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ የተሻለ የፖሊስ አገልግሎትን በትብብር እና በቅንጅት መስጠት በሚያስችል ጉዳዮች ላይ ከመግባባት መደረሱንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ረገድ የተሻሉ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፤ ይህን ስራ በሁሉም ክልሎች ለማስፋት በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡም ዜጎች በሞባይል ስልካቸው አማካኝነት ከፖሊስ ጋር መረጃ መለዋወጥ የሚችሉበት መተግበሪያ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።