የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽኖች የመሪዎችና የአመራር አካዳሚ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፦ የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽኖች የመሪዎችና የአመራር አካዳሚ ጉባኤ በሚቀጥለው ሣምንት በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው። 

ጉባኤው ከመስከረም 07/2016 ዓ.ም ጀምሮ ሦስት ተከታታይ ቀናት የሚሄድ ሲሆን ከ39 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ የዘርፉ ተዋናዮችና ሌሎች እንግዶች በጉባኤው ይሳተፋሉ ተብሏል።

የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ይህንን ጉባኤው የተሳካ ለማድረግና በቀጣይ በሌሎች ጉዳዮች በትብብር ለመሥራት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ዛሬ ሥምምነት ፈጽሟል።

ሥምምነቱን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቀናጀ የማርኬቲንግ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ንጉሱ ወርቁና የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ቻርለስ ንያምቤ ፈርመውታል።

የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ምህረት ንጉሴ የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽኖች የአመራርና የአካዳሚ ጉባኤን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።


 

በጉባኤውም በዓለም አቀፍ የስፔሻል ኦሊምፒክ ሕግጋት፣ አሰራሮችና በተካሄዱ ውድድሮች ላይ የነበሩ ጥንካሬን ድክመቶች ላይ በመምከር የቀጣይ ማሻሻያ ርምጃ እንደሚቀመጥ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ፈሪድ መሃመድ፤ በጉባኤው የተገኙ አዳዲስ ልምዶች ላይ ምክክር በማድረግ የአዕምሮ ውስንነት ተጠቂ የሆኑ ዜጎችን ስፖርታዊ ተሳትፎ ማሳደግ የጉባኤው ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቀናጀ የማርኬቲንግ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ንጉሱ ወርቁ፤ ሥምምነቱ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ጉባኤ የሚታደሙ ተሳታፊዎችን ማጓጓዝ፣ የስካይ ላይት ሆቴል መስተንግዶና ሌሎች ቀጣይ ትብብሮችን ያካትታል ነው ያሉት።


 

የአፍሪካ ስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ቻርለስ ንያምቤ፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተደረሰው ሥምምነት ጉባኤውን በስኬት ለማስተናገድ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።


 

የስፔሻል ኦሊምፒክ ፌዴሬሽን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1968 የተመሰረተው ሲሆን የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች በስፖርታዊ ውድድሮች የሚያበረታታ ስፖርታዊ የውድድር አይነት ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም