ቀጥታ፡

የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ ሊተገብር ይገባል-የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፦ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ ሊተገብር እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ። 

ሚኒስቴሩ ህብረተሰቡ የወባ በሽታ ስርጭት ቀንሷል በሚል መዘናጋት የመከላከል መንገዱን በአግባቡ እየተገበረ አለመሆኑንም ገልጿል። 

ከመስከረም 6 ቀን 2016 እስከ መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄደውን ዘጠነኛው የመላው አፍሪካ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ማህበር  ዓመታዊ  ጉባኤና አውደ-ርዕይ አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴርና የማህበሩ ኃላፊዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኑኬሽን ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ እንዳሉት፤ የወባ በሽታ ከጤና እክልነቱ ባሻገር በአገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ጉዳት የሚያደርስ የእድገት እንቅፋት ነው። 

በአለም አቀፍ ደረጃ በወባ ከሚያዙ ሰዎች መካከል 95 በመቶ እንዲሁም ከሚሞቱ ሰዎች መካከል ደግሞ 96 በመቶ በአፍሪካ የሚገኙ መሆኑን አንስተዋል። 

በኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት በወባ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር በ90 በመቶ መቀነስ መቻሉን አስታውሰው፤ ሆኖም ባለፉት ሁለት ዓመታት የበሽታው ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል።

ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ምክንያቶች ለስርጭቱ መጨመር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ የአየር ንብረት ለውጥና የፀጥታ ችግር ከእነዚህ መካከል መሆናቸውን አንስተዋል። 

የበሽታውን የመቀነስ አዝማሚያ በማየት ወባ ጠፍቷል የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝም በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።

በተለይ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ባሉት ጊዜያት የወባ በሽታ ስርጭት የሚጨምር መሆኑን በመገንዘብ ህብረተሰቡ  ከወዲሁ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ጉባኤው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑም ተናግረዋል። 

በመላው አፍሪካ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ማህበር  የኢትዮጵያ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው በበኩላቸው እንደ አገርም ሆነ እንደ አህጉር የውሃና ትንኝ ወለድ በሽታዎች ስርጭት እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

ማህበሩ በአህጉር አቀፍ ደረጃ እ.አ.አ 2011 በዘርፉ ባለሙያዎች የተመሰረተ መሆኑንና  በወባ በሽታ ላይ ቅኝትና ምርምር የሚያደርግ አህጉር አቀፍ ማህበር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ደረጃ በ2021 ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል። 

በጉባኤው ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉ ሲሆን ጉባኤው በባለሙያዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የባለፈው አመት ተመሳሳይ ጉባኤና አውደ-ርዕይ በሩዋንዳ የተካሄደ ሲሆን የቀጣዩን ዓመት ጉባኤ ኮትዲቯር ታስተናግዳለች።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም