ቀጥታ፡

ጌዴኦ ዞን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል- የዞኑ አስተዳደር

ዲላ (ኢዜአ) መስከረም 4/2016-በጌዴኦ ዞን በተያዘው ዓመት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በዞኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በርካታ ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን ጠቅስዋል።

በአጼ ዳዊት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጌዴኦ ልማት ማህበር በአጭር ጊዜ ውስጥ አስገንብቶ ለአገልግሎት ያበቃቸውን አራት የመማሪያ ክፍሎች ጨምሮ በተለያዩ አካላት በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውንም ለአብነት አንስተዋል።

ሁለንተናዊ እድገት ማስመዝገብ የሚቻለው በትምህርት ብቻ መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው በዞኑ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በተቀናጀ መንገድ የሚደረገው ጥረት እንደሚጠናከር ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ውጤታማ ተማሪዎችን ለማፍራት በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለዚህም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ጎን ለጎን የትምህርት ግብዓቶችን ለማሟላት፣ የመምህራንን አቅም ለመገንባትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል እንደሚሰራም አስረድተዋል።

በዞኑ በሚገኙ 270 ትምህርት ቤቶች ከ274 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለመማር ማስተማር ሥራ ወደ ተግባር መገባቱን ያነሱት አስተዳዳሪው ህብረተሰቡ በተለይ ወላጆች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩም ጥሪ አስተላልፈዋል።


 

የዲላ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ዘመናይ ህርባዬ በበኩላቸው በከተማው ለመቀበል ከታቀደው ከ37 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ ዛሬ ከ20 ሺህ የሚልቁት ምዝገባ አጠናቀው በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በዛሬው ዕለት በከተማው በሚገኙ ሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ የተጀመረ ሲሆን የቀሩት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት የቤት ለቤት ምዝገባ መጀመሩን አስረድተዋል።

ወይዘሮ ዘመናይ አክለውም ወላጆች ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ታዳጊዎችን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ትምህርት ቤቱ በተሻለ ደረጃ ታድሶና ተገንብቶ እንዲሁም የተማሪዎች መቀመጫ ተሟልቶለት በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የአጼ ዳዊት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ዕዝራ ወርቁ ነው።

በተለይ እርሱ የሚገኝበት የመማሪያ ክፍል እንደ አዲስ የተገነባ በመሆኑና በመጀመሪያው የትምህርት ቀንም በርካታ ጓደኞቹን በማግኘቱ ለመማር ያለው መነሳሳት መጨመሩን ተናግሯል።

በተያዘው የትምህርት ዘመን ትምህርቱን በአግባቡ በመከታተልና በርትቶ በማጥናት ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደሚጥርም ገልጿል።

በማስጀመሪያ መረሃ ግብሩ ላይ የዞንና የከተማ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ መምህራንና የተማሪ ወላጆች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም