ቀጥታ፡

የተሰጠንን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ስርዓት በማስያዝ መሬታችንን በአግባቡ ለመጠቀም ችለናል- በአልብኮ ወረዳ አርሶ አደሮች

ደሴ፤  መስከረም 4 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- የተሰጣቸው  የይዞታ  ማረጋገጫ ካርታ  ስርዓት በማሲያዝ መሬታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በደቡብ ወሎ ዞን  አልብኮ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በደቡብ ወሎ ዞን ለ211 ሺህ 974 አርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን የዞኑ መሬት መምሪያ አመልክቷል።

ከአልብኮ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል የቀበሌ 04 ነዋሪው አቶ ግርማ መሰለ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም የማሳ ወሰን በትክክል የሚታወቅ ባለመሆኑ ጉልበተኞች ይዞታቸውን በመጋፈት ይነጥቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰጣቸው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ስርዓት በማስያዝ መሬታቸውን በአግባቡ ለመጠቀምና ለማልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም ይዞታቸውን በህግ አግባብ በማስያዝ ገንዘብ ለመበደር፣ ዋስ ለመሆንና ልጆቻቸውን በቀላሉ ለማውረስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላዋ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅዬ ሙሄ፤ ፤ የመሬት ይዞታችን ወሰን በውል ባለመታወቁና ተጨባጭ ሰነድ ባለመኖሩ በሙሰኞች እየተነጠቅን ነበር ብለዋል፡፡

ስርዓት የያዘ ባለመሆኑ ያለመግባባት ችግር ይገጥማቸው እንደነበረም ጠቅሰው፤ አሁን የተሰጠው ካርታ ችግሩን የፈታና በተለይም የሴቶችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

የአልብኮ ወረዳ መሬት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሩ ይማም ፤ የመሬትን ህገ ወጥ ወረራና አለመግባባትን ለማስቀረት ለማስቀረት የይዞታ ማረጋጋጫ ካርታው የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ በወሰን መገፋፋት ምክንያት ይደርስ የነበረውን ጉዳት፣ በክስ ፍርድ ቤት ማጨናነቅና ተያያዥ ችግሮችን ከማስቀረቱ ባለፈ በሴቶች ላይ ይፈጸም የነበረው የመሬት መንጠቅና ማጭበርበርን መከላከል መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በወረዳው ከየካቲት 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገ ጥረት 10 ሺህ ለሚጠጉ አርሶ አደሮች ሁለተኛ የይዞታ ካርታ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በተያዘው የበጀት ዓመትም ለ10 ሺህ አርሶ አደሮች በተመሳሳይ ለመስጠት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

በወረዳው እስካሁን ከ67 ሺህ የሚበልጥ ማሳ ሁለተኛ ይዞታ ካርታ ለአርሶ አደሩ መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን መሬት መምሪያ የገጠር መሬት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ምሳው አክቤ በበኩላቸው ፤ በዞኑ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ211 ሺህ 974 አርሶ አደሮች ሁለተኛ ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡


 

ካርታ የወሰዱ አርሶ አደሮች ብድር መውሰድ መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ በ2015 ዓ.ም ብቻ 204 አርሶ አደሮች ካርታቸውን አስይዘው 29 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ ተቋማት ተበድረው መጠቀም ችለዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም