በክልሉ ለሕዳሴው ግድብ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው--ጽህፈት ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለሕዳሴው ግድብ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው--ጽህፈት ቤቱ
ባህር ዳር፤(ኢዜአ) መስከረም 4/2016፡-በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ከህዝብ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የሕዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሀይለሚካኤል ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት በቅርቡ አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት በስኬት የተከናወነው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠናቀቅ መላው ህዝብ በቀጣይም ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል።
ባለፉት 12 ዓመታት የክልሉ ህዝብ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ በመፈጸም አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰው፤ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች በመሳተፍም ለግድቡ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የግድቡን ግንባታ ፈጥኖ በማጠናቀቅ ሀገርና ህዝብ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተያዘው ዓመትም ህብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች ለግድቡ ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።
"በክልሉም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነትን ለማሳደግ ግድቡን ዳር ማድረስ ያስፈልጋል" ሲሉም ተናግረዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የሕዳሴው ግድብ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚፈጠረውን ቀጠናዊ ትስስር በማጠናከር በጋራ ለማደግ፣ ፍትሃዊ አጠቃቀምን ለማስፈንና ለገጽታ ግንባታ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
እንደ ሃላፊው ገለጻ የሕዳሴው ግድብ ተጠናቆ የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ በበጀት ዓመቱ በአማራ ክልል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከህዝብ በማሰባሰብ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
እቅዱን ለማሳካት የመንግስት ተቋማት፣ የብዙሃንና የሙያ ማህበራት እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች አደረጃጀቶችን በማነቃነቅ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
"በተለይም የወጣትና ሴት አደረጃጀቶችን እስከ ቀበሌ ድረስ በማነቃነቅ ዕቅዱን ለማሳካት ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።
የመንግስት ሠራተኛው አቶ አስማረ ሃይሌ በበኩላቸው ግድቡ ከተጀመረ ጀምሮ በተለያዩ ዓመታት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የወር ደመወዛቸውን ቦንድ በመግዛት ሲደግፉ እንደነበር ጠቅሰው፣ እስካሁን ድረስ ከ8 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከአገር ፍቅር፣ በዓባይ ወንዝ ላይ ከነበራቸው ቁጭት እና ሀገራዊ የልማት ጉዞ እንዲሳካ ካላቸው ፍላጎት ተነስተው በቀጣይም ቦንድ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
እንደ ሀገር በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም የግድቡ አራተኛ እና የመጨረሻ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ሲሰሙ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም አቶ አስማረ ጠቁመዋል።
በክልሉ በ2015 በጀት ዓመት ለሕዳሴው ግድብ ከ17 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመሰብሰብ ድጋፍ መደረጉን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለከታል።