በኦሮሚያ ክልል በክረምቱ ወራት ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረጃ ማሻሻል ስራ ተሰርቷል-የክልሉ ትምህርት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በክረምቱ ወራት ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረጃ ማሻሻል ስራ ተሰርቷል-የክልሉ ትምህርት ቢሮ

አዳማ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል በክረምቱ ወራት ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረጃ ማሻሻል ስራ ሲሰራ መቆየቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ አስታወቁ።
በክልሉ የዘንድሮው የመማር ማስተማር ፕሮግራም መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀምርም ገልጸዋል።
ዶክተር ቶላ በሪሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከሚገኙት ከ27 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች መካከል 23 ሺህ የሚሆኑት የደረጃ ማሻሻያ ስራዎች ይፈልጋሉ።
በክረምቱ ወራትም በ3 ሺህ 410 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረጃ ማሻሻል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በተሰራው ስራም ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መፅሐፍቶች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ ውሃ አቅርቦት፣ መብራትና መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ መከናወኑን ገልጸዋል።
የደረጃ ማሻሻያ ስራው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የክልሉን ተወላጆችን፣ ባለሃብቶችንና መላውን ህብረተሰብ በማስተባበር መከናወኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶችን በተገቢው የመማሪያ ግብዓትና ቁሳቁስ ከማደራጀት ባለፈ ፅዱና ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን አስረድተዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ከ4 ሺህ በላይ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
በተያያዘም የዘንድሮው የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ከነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ እየተካሄደ አንደሆነም ጠቁመዋል።
በእስከ አሁኑ ሂደት ከ9 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸው በዘንድሮው ዓመት 11 ሚሊዮን ተማሪዎች ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ ትምህርት ላይ ይሆናሉ ብለዋል።
በክልሉ የዘንድሮው የመማር ማስተማር ስራውን ከመስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ይጀመራል ያሉት ዶክተር ቶላ በአርብቶ አደር አካባቢዎች መጪው ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም ለማስጀመር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርም በክልሉ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ መታቀዱን ተናግረዋል።