የፌዴራል፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች 15ኛ የጋራ ጉባኤና አገር አቀፍ ገለልተኛ የፖሊስ አማካሪ ምክር ቤት ጉባኤ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች 15ኛ የጋራ ጉባኤና አገር አቀፍ ገለልተኛ የፖሊስ አማካሪ ምክር ቤት ጉባኤ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፦ የፌዴራል፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች 15ኛ የጋራ ጉባኤና አገር አቀፍ ገለልተኛ የፖሊስ አማካሪ ምክር ቤት ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤልን ጨምሮ፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ባካሄዳቸው የለውጥ ስራዎች በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራና በተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት አያያዝ ውጤታማ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአገር ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትን መከላከል መቻሉን አመልክተዋል።
ከጎረቤት አገራት ጋር በመቀናጀትም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመከላከል ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
በፖሊስ ስራ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያሻሽል አካታችነት መተግበሪያ የማበልጸግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ስራን የማዘመኑ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በአዲሱ ዓመት ፖሊስ ከሕዝብ ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር የአገርን ሰላምና ደህንነት ለማስፈን እንደሚሰራም ነው የገለጹት።