ቀጥታ፡

ዘጠነኛው የመላው አፍሪካ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2016 (ኢዜአ) ፦ ዘጠነኛው የመላው አፍሪካ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤና አውደ ርዕይ ከመስከረም 6 እስከ 10/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ጉባኤው "በየጊዜው እየታዩ ባሉ ትንኝ ወለድ በሽታዎች ሥጋት ላይ የሚደረግ ክትትልና አስተዳደርን መልሶ ማጤን" በሚል መሪ ኃሳብ ይከናወናል።

በጉባኤው ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ እስከ አንድ ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስቴርና የመላው አፍሪካ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ማኅበር ጉባኤውን አስመልክቶ የጋራ መግለጫ ዛሬ ሰጥተዋል።

የማኅበሩ የኢትዮጵያ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው በመግለጫው፤ ጉባኤው የወባ በሽታን ለመከላከል የተሰሩ ሥራዎች ላይ ይመክራል ብለዋል።

የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ በበኩላቸው ጉባኤው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማከናወን የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጉባኤና አውደ ርዕይ በሩዋንዳ የተካሄደ ሲሆን የቀጣዩን ዓመት ጉባኤ ደግሞ ኮትዲቯር ታስተናግዳለች ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም