ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ልዩ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡናዋን ለዓለም እያስተዋወቀች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ልዩ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡናዋን ለዓለም እያስተዋወቀች ነው
አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ልዩ ጣዕምና ጥራት ያለው ቡናዋን ለዓለም እያስተዋወቀች መሆኗን በኳታር የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፈይሰል አልይ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት በኳታር ዶሃ በሚካሄደው ዓለም ዓቀፍ ልዩ የቡና ትርኢት ላይ እየተሳተፈች ነው።
አምባሳደር ፈይሰል የቡና ትርኢቱ አምራችና ገዢዎችን በቀጥታ ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ልዩ ጣዕም፣ ጥራትና ብዙ አይነት የሆነውን ቡናዋን ለዓለም በተለይም ለኳታር ህዝብ የምታስተዋውቅበት መድረክ እንደሆነም አስረድተዋል።
በኳታር የሚገኙ ቡና አስመጪ ኩባንያዎች ምርቶቻችንን አይተው በቀጥታ እንዲገዙ ግንኙነት ለመመስረት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ብለዋል።
በንግድ ትርዒቱ የተሳተፉት የቡና አምራች ኩባንያዎች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑና የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር ይህንን የንግድ ትርዒት እንደ አንድ አማራጭ መጠቀማቸውን ጠቅሰዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ዓለም ዓቀፍ ልዩ የቡና ትርኢት ቡና በማቀነባበር፣ በማልማት፣ በማምረት፣ በመሸጥ እና ተያያዥ ዘርፎች የተሰማሩ የተለያዩ ሀገራት የንግድ ድርጅቶች እየተሳተፉ መሆኑን ከኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።