የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር የሚገነባ ትውልድ የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- የትምህርት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር የሚገነባ ትውልድ የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- የትምህርት ቢሮ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2016(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር የሚገነባ ትውልድ የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ገለጹ።
የትምህርት ቢሮው ''የጋራ መግባባት ለውጤታማ መማር ማስተማር'' በሚል መሪ ሃሳብ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ዝግጅት አስመልክቶ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ቡድን መሪዎች፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐር-ቫይዘሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፤ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት በሥነ-ምግባር የታነጸ ሀገር የሚገነባ ትውልድ የመፍጠር ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።
በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ምቹና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥርዓት እንዲኖር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመማር ማስተማር ሂደቱ ባለድርሻ አካላትና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ለትምህርት ጥራት፣ ተደራሽነትና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ የትምህርት ተቋማት ከየትኛውም የጸጥታ ስጋት ነፃ ሆነው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራቸውን በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉ ርዕሳነ-መምህራን እና ሱፐር-ቫይዘሮች በአዲሱ የትምህርት ዘመን ውጤታማና ሰላማዊ መማር ማስተማር ሥርዓትን ለማስቀጠል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በመዲናዋ የሚገኙት ከ2 ሺሕ 200 በላይ ትምህርት ቤቶችም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው በማስተናገድ የመማር ማስተማር ስራቸውን የሚያከናውኑ መሆኑ ተገልጿል።
አዲሱ የትምህርት ዘመን መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም የሚጀመር መሆኑን የትምህርት ቢሮ መግለፁ ይታወቃል።