የኢትዮጵያን የወደብ አማራጮች ማስፋት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር ነው - በስዊድን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የወደብ አማራጮች ማስፋት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጠናክር ነው - በስዊድን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚነት አማራጮች ማስፋት በቀጣናው አገራት ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጎልበት የላቀ ፋይዳ እንዳለው በስዊድን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት ያሲን አህመድ ገለጹ።
በዓለም ላይ የባህር በር ከሌላቸው 44 አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን በርካታ የህዝብ ቁጥር ይዛ የባህር ወደብ የሌላት ሀገር መሆኗም ይታወቃል።
በመሆኑም የወደብ አማራጮችን በማስፋት ራሷን ተጠቃሚ ከማድረግም ባለፈ ቀጣናዊ ትስስርን ለማሳለጥ እየሰራች ትገኛለች።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በስዊድን የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት ያሲን አህመድ፤ የአፍሪካ አገራት የተለያዩ ስምምነቶችን በማድረግ የወደብ አማራጮችን ለማስፋት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአገራቱ መካከል ሩዋንዳ ከኬንያ እንዲሁም ማሊ ከሴኔጋል ጋር ስምምነቶችን በመፈራረም ወደቦችን የመጠቀም ተሞክሮ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያም በጋራ የመልማት ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደብ ካላቸው አገራት ጋር የረጅም ጊዜ ስምምነቶችን ማድረግ ይጠበቅባታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት አማራጭ ወደቦችን የመጠቀም ፍላጎት ሕጋዊና ተገቢ ሆኖ ከራስም ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር መሳለጥ አይነተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የወደብ አጠቃቀም የማስፋት ሕልሞች ዓለም አቀፍ የባህር ሕግ ስምምነትን የተንተራሰና የባህር በሮችን የመጠቀም መብት የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ወደቦችን በመጠቀም ከምታገኛቸው ጥቅሞች ባሻገር በንግድና ሌሎችም የልማት ትስስሮች የሌሎች አገራትን ተጠቃሚነትም የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጉልህ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ባለሀብቶችም የወጪና የገቢ ንግድ ስራቸውን በቀላሉ ለመከወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ንግዷ አማራጭ ወደቦችን የማብዛት ስራዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት ነው ያሉት።
በ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ በተቀመጠው መሰረት ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ ዘርፍ ያላትን አቅም ለማሻሻል እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።
በእቅዱ መሰረትም በ10 ዓመታት ሰባት ወደቦችንና 12 ኮሪደሮችን በመጠቀም የወደብ አማራጮችን ለማስፋት እየተሰራ ይገኛል።
በጋራ ወደቦችን በማልማት ከጎረቤት አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።