ቀጥታ፡

20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ይካሄዳል - የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2016(ኢዜአ)፦ 20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።


በዚሁ ጊዜም የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡና ሳምንት የሚካሄድ መሆኑም ተመላክቷል።

ባለስልጣኑ የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ጉባኤ ዝግጅትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ቡና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ የግብርና ዘርፍ ነው።

የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ መደረጉም የኢትዮጵያ ቡና በአፍሪካ እና በዓለም ገበያ ይበልጥ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።


 

የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽንም ከፊታችን ጥር 28  ጀምሮ ለ4 ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጉባኤው "Speciality Coffee at Origin" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ በጉባኤና ኤግዚቢሽኑም ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች፣ ምሁራንና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚታደሙ ተናግረዋል።

ጉባኤው እና ኤግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ በኢንተር አፍሪካን ኮፊ ኦርጋናይዜሽን እና የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም ቡናዎች ማህበር የሚዘጋጅ መሆኑንም ተገልጿል።

ጉባኤው 2ሺህ የሚጠጉ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ የቡና ቆይዎች፣ ነጋዴዎች፣ አምራቾች፣ ገዥዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎችን በአንድ ጣሪያ ስር በማሰባሰብ ዘላቂነት ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ፖሊሲዎች ላይ የውይይት የሚካሄድ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም