ለሕጻናት ተማሪዎች የሚደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በትምህርት ቤት ምገባ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሕጻናት ተማሪዎች የሚደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በትምህርት ቤት ምገባ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ድሬዳዋ እና ሰመራ (ኢዜአ) መስከረም 3/2016-ሕጻናት በትምህርት ቁሳቁስ ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ የሚደረገው ድጋፍ በትምህርት ቤት ምገባ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
የትምህርት ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ወላጆቻቸው አቅም የሌላቸው ህፃናት በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ እያደረጉ ያሉት ድጋፍ አበረታች ነው።
ኢትዮ-ቴሌኮም የምስራቅ ሪጅን በቢሮው በኩል 1 ሺህ 453 ደርዘን ደብተሮችን ለሕጻናት ድጋፍ በማድረጉ አመስግነው፣ ድጋፉ በትምህርት ቤት የምገባ መርሃ-ግብር እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የድሬዳዋ አስተዳደርና የፌደራል ተቋማት ድጋፍ ለሚሹ ህፃናት እያደረጉት ያሉው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
"የወደፊት አገር ተረካቢ ህጻናት በችግር ሳቢያ ከትምህርት ገበታቸው እንዳይለዩ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ምስራቅ ሪጅን የኢንተርፕራይዝ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ለማ በበኩላቸው ሪጅኑ ለተማሪዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የምስራቅ ሪጅን ዋና መስሪያ ቤት ለድሬዳዋ ህፃናት ካበረከተው 1ሺህ 453 ደርዘን ደብተሮች በተጨማሪ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ለሚገኙ ቀርሳና ጨለንቆ ወረዳዎች 500 ደርዘን ደብተሮችን አበርክቷል ብለዋል።
በዛሬ ዕለት ለጭሮ ወረዳ 500 ደርዘን ደብተር መሰጠቱንና በነገው ዕለት ደግሞ 447 ደርዘን ደብተር በሶማሌ ብሔራዊ ክልል ለሲቲ ዞን ይለገሳል ብለዋል።
በተጨማሪም ድሬዳዋ ለሚገኘው "አሰገደች አረጋውያን መጦሪያ ማዕከል" 178 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን አቶ ቴዎድሮስ አስታውቀዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ ድሬዳዋን ጨምሮ ለምስራቅና ለምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች እና ለሲቲ ዞን ግምታቸው 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ደብተሮች ከ4ሺህ ለሚበልጡ ተማሪዎች ድጋፍ እየተደረገ ነው።
ድጋፍ ከተደረገላቸው የድሬዳዋ ተማሪዎች መካከል የ6ተኛ ክፍል ተማሪ መገርቱ ሁሴን፤ "የደብተር ዋጋ እየተወደደ በመምጣቱ ድጋፉ ችግራቸውን ከማቃለል ባለፈ በርትቶ ለመማር እንደሚያግዛቸው ገልጻለች።
"ዛሬ የተሰጠኝ መማሪያ ደብተር ዘንድሮ ስለደብተር ሳላስብ ለመማር ያስችለኛል" ያለው ደግሞ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ኤርሚያስ ሀብታሙ ነው።
በተመሳሳይ ዜና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠመራ ቅርንጫፍ ለወረር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 100 ደርዘን ደብተር ድጋፍ አድርጓል።
የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሲን ዓሊ ድጋፍ በተደረገበት ወቅት እንደገለጹት፣ ድጋፍ የሚያሻቸውን ተማሪዎች ማገዝ ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው።
አገልግሎቱ በቀጣይም ድጋፉን በማጠናከር በሁለት ወረዳዎች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሰል ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ድጋፍ የተደረገለት የወረር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
የበዓሉ የዝግጅት ኮሚቴ አባል የሆኑት የአፋር ክልል ገጠር መሬት አጠቃቀምና መሬት አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኀላፊ አቶ አህመድ ኢብራሂም፣ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው እርስ በርስ የመረዳዳቱ ተግባር የቆየ እሴት በመሆኑ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።