የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ 307 ታዳጊዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን መዘጋጀቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በዘንድሮው ዓመት 307 ታዳጊዎችን ተቀብሎ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለማሰልጠን መዘጋጀቱን የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው ገለጹ።

በየዘርፉ ተመልምለው ለስልጠና የሚገቡ ስፖርተኞች ለአራት ዓመታት ስልጠና የሚሰጣቸው መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ሀገርን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች የሚወክሉ ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን በሳይንሳዊ ስልጠና በመታገዝ የማፍራት ተልዕኮ ይዞ እየሰራ ይገኛል።


 

በ24 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው አካዳሚው በውስጡ ስታዲየም፣ ጅምናዚየም፣ የመማሪያና የመኝታ ክፍሎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ የመዋኛ ገንዳ ያለው ነው።

ከአስር ዓመት በፊት በ290 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው አካዳሚው በየዓመቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ታዳጊ ስፖርተኞችን በመመልመል ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

በአካዳሚው ሰልጥነው ስኬታማ ከሆኑ ስፖርተኞች መካከልም አትሌት ለሜቻ ግርማ (አትሌቲክስ)፣ ሰለሞን ቱፋ (በወርልድ ቴኳንዶ) እና  ናርዶስ ሲሳይ (በማርሻል አርት) ይጠቀሳሉ።

በ2016 ዓ.ም አካዳሚው በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች 307 ስፖርተኞችን በመመልመል ለማሰልጠን ዝግጅት ማድረጉን የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው ገልጸዋል።

ከሚሰለጥኑባቸው የስፖርት አይነቶች መካከልም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌት፣ ቅርጫት ኳስ እና ሌሎችንም ጠቅሰዋል።


 

በመሆኑም እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ 3 ሺህ ታዳጊዎች መመዝገባቸውን አስታውሰው በተቀመጠው መስፈርት መሰረት 307ቱ ተለይተው ወደ አካዳሚው ለስልጠና ይገባሉ ብለዋል።

ለስልጠና የሚገቡ ታዳጊዎች የሚለዩትም በእድሜ፣ በአካል ብቃት፣ በጤንነት ሁኔታ እና በስነ ልቦና ዝግጁነት መሆኑን ዘርዝረዋል። 

በዚህ መሰረትም የመጨረሻ የማጣሪያ ምልምላ ያለፉት ታዳጊዎች ለቀጣይ አራት ዓመታት በአዲስ አበባ እና በአሰላ ስፖርት አካዳሚ ይሰለጥናሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ካሰለጠናቸው ታዳጊዎች መካከል ከ250 በላይ ስፖርተኞችን በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ለብሄራዊ ቡድን ማስመረጡን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም