ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት 119 የምርትና ግብዓት ደረጃዎችን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት 119 የምርትና ግብዓት ደረጃዎችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2016(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት 119 የምርትና ግብዓት ደረጃዎችን ማጽደቁን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ አቶ ብሩክ ሃብቴ በሰጡት መግለጫ፤ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ፣ የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት የሚጠብቁና ከባቢያዊ ደህንነትን ያገናዘቡ ደረጃዎችን የማውጣት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒካል ኮሚቴ በተለያዩ ዘርፎች 312 ደረጃዎችን ለማጸደቅ አዘጋጅቶ ለብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱም ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 37ኛ መደበኛ ስብሰባ ከቀረቡለት ደረጃዎች ውስጥ 119ኙን መርምሮ ማጽደቁን ነው ያብራሩት።
የጸደቁት ደረጃዎች ከፊሎቹ አዳዲስ ሲሆኑ ከፊሎቹ ደግሞ የማስተካከያ ክለሳ የተደረገባቸው ናቸው ብለዋል።
ከጸደቁት መካከል የምግብና የግብርና ውጤት ዘርፍ 52 ደረጃዎች፣ በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች 23 ደረጃዎች እንዲሁም በኤሌክትሮ መካኒካል ዘርፍ 44 ደረጃዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የጸደቁት ደረጃዎች ጥራት ያላቸው ምርቶችና ግብዓቶችን ለገበያ ለማቅረብ ፤ ጤናማ የንግድ ውድድርን ለማጎልበት እንደሚያግዙ ነው ያስረዱት።
ለእውቀት ሽግግርና ለምርምር የሚውሉ ግብዓቶችን ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩም ታምኖባቸዋል ብለዋል።