የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚያደርጉትን ሚና የበለጠ ማጠናከር አለባቸው- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚያደርጉትን ሚና የበለጠ ማጠናከር አለባቸው- የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2016(ኢዜአ)፦የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተፈጠረውን ምቹ መደላድል በመጠቀም ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለፀ።
ባለስልጣኑ በአገሪቱ ከለውጡ ማግስት በተፈጠረው ምቹ መደላድል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱንም ገልጿል።
የተደረጉ የህግ ማሻሻያዎችና የተፈጠረው ምቹ ምህዳር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና በዲሞክራሲ ላይ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የሚያስችል መሆኑ ይነገራል።
አሁን በአገሪቱ ህጋዊ እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ከ4 ሺህ 700 በላይ የሲቪል ማህበራት እንደሚገኙም እንዲሁ።
ሆኖም ከተፈጠረው ምቹ ምህዳር፣ አገር ከምትፈልገውና ከላቸው ቁጥር አንጻር እያደረጉት ያለው አስተዋፅኦ በቂ ባለመሆኑ የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ባለስልጣኑ ጠይቋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ባለፉት አራት ዓመት ተኩል በሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ የተደረጉ ማሻሻያዎች ዘርፉ እንዲያድግ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልፀዋል።
በተደረገው ማሻሻያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱንም አያይዘው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከ10 ያልበለጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዲሞክራሲ ዙሪያ ይሰሩ እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ ሁሉም ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዲሞክራሲ ላይ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዲሞክራሲ ግንባታ፣ በግጭት አፈታትና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተለያዩ ስራዎች ሲከውኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የዲሞክራሲ ባህል እንዲጎለብት የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ህብረተሰቡ የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያደርግ ሲሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።
ሆኖም ከተፈጠረው ምቹ ምህዳርና አገር ከምትፈልገው አንፃር ያደረጉት አስተዋፅኦ በቂ ባለመሆኑ የበለጠ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት የህግና ፖሊሲ ጉዳዮች አማካሪ ዘላለም እሸቱ ለኢዜአ እንዳሉት በልማት ዲሞክራሲና ሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ 4 ሺህ 700 የሲቪል ማህበራት በምክር ቤቱ ስር ይገኛሉ።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዜጎች ስለዲሞክራሲ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፕሮ ዴቨሎፕመንት ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አህመድ ሁሴን በበኩላቸውተቋሙ በልማትና ዲሞክራሲ ዙሪያ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲቪል ማህበራት የዲሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባትና ባህሉን ለማሳደግ ሚናቸው የጎላ እንደሆነ ገልፀው ድርጅታቸው ይህ በመገንዘብ ለሰላም ግንባታ የሚረዱ የማህበረሰብ ውይይቶች ሲያካሂድ መቆየቱን አብራርተዋል።