የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን በቀጣይም አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩ የጎላ ሚና አለው - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን በቀጣይም አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩ የጎላ ሚና አለው - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች
ዲላ፤ መስከረም 3/2016 (ኢዜአ) --የሕዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን አብሮነት በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጎላ ሚና እንደሚኖረው የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ እንደ ሀገር የገጠሙ የውስጥና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም የውሃ ሙሌት ሥራው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ሲሰሙ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ዜና ክፍሌ እንዳሉት በሕዳሴው ግድብ የተለያዩ ጫናዎች ቢኖሩም ህዝብና መንግስት ባሳዩት ቁርጠኝነት ግድቡ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
አራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራው በስኬት መጠናቀቁን ሲሰሙ ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል።
"ግድቡ እውን እንዳይሆን ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎችን በአብሮነትና በዓላማ ጽናት አልፈናል" ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፣ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን አብሮነትን በማጠናከር ለሌላ የልማት ሥራ እንዲነሳሱ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በተለይ በአዲሱ ዓመት ህብረትን የሚሸረሽሩ ነገሮችን በማስወገድ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ወይዘሮ ዜና ተናግረዋል።
"የሕዳሴው ግድብ እውን ለማድረግ ዜጎች ያሳዩትን ጥንካሬና ጽናት በአዲሱ ዓመትም በሌሎች የልማት ዘርፎች መድገም ይገባል" ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ በሙሉ አቅም የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት እስኪጀምር ድረስ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ወይዘሮ ዜና አረጋግጠዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ታምራየሁ አድማሱ በበኩላቸው ሁሉም ዜጎች ካላቸው ጥሪት ላይ ባዋጡት ገንዘብ የተገነባው የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ሲሰሙ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
"ባለፉት ዓመታት እንደሀገር የገጠሙ የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቁ የእኛን ጥንካሬና ያቀድነውን መፈጸም እንደምንችል ያሳያል" ብለዋል።
በተለይ ኢትዮጵያዊያን የአይቻልምን መንፈስ የሰበሩበት፤ በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ያረጋገጡበት በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አቶ ታምራየሁ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ በየዓመቱ ስኬታማ ለውጥ እያሳየ መምጣት ለሌላ የልማት ሥራ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ለማጠናከር ሚናው የጎላ ነው።
የግድቡ የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅ ኢትዮጵያዊያን በህብረት ከተነሳን ያቀድነውን ማሳካት እንደምንችል በተጨባጭ የሚያሳይ ነው" ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አቶ መስፍን በሾ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው።
እንደአቶ መስፍን ገለጻ ፈተና ቢኖርም ለአንድ ዓላማ በጋራ መቆም ከተቻለ ግዙፍ የልማት ሥራዎችን ማሳካት እንደሚቻል በሕዳሴው ግድብ ለዓለም ማሳየት ተችሏል።
የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባዋጡት ገንዘብ ግድቡ እውን መሆኑ እንዳስደሰታቸው አቶ መስፍን ጠቁመው፣ በአዲስ አመት መባቻ የውሃ ሙሌት ስራው መጠናቀቅ መበሰሩ ዜጎችን ለተጨማሪ የልማት ውጤት እንዲነሳሱ ያደርጋል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቁ በአዲስ ዓመት ዋዜማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ መደረጉ የሚታወስ ነው።