ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኮሪያ ሪፐብሊክ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 2/2016 (ኢዜአ)፡-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኮሪያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ።
አቶ ደመቀ ልዩ መልዕክተኛውን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት እንደገለጹት በደም የተሳሰረውን የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ለማጠናከር ሁነኛ ጊዜ ላይ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል።
ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በቴክኖሎጂ ልማት እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ያላትን የካበተ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ትብብሯን እንድታጠናክርም ጠይቀዋል።
በኮሪያ ሪፐብሊክ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እየከታተሉ ያሉ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም በመጥቀስ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለኮሪያ አንዷ መዳረሻ መሆኗንም አስታውሰዋል።
በተጨማሪም የኮሪያ ሪፐብሊክ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶች እንዲሰማሩባቸው ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ባለችባቸው እንደ ግብርና፣ ማምረቻ፣ ማዕድን ልማት፣ ቱሪዝም እና ችግር ፈቺ ፈጠራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የኮሪያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልዩ መልዕክተኛ ሀክ ቺዮል ሺን በበኩላቸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያ ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።
አክለውም ሀገራቸው በፋርማሲዩቲካል ማምረቻ እና በግብርና ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላት ጠቁመው የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ባለሀብቶች እንዲሰማሩባቸው ቅድሚያ ሰጥቶ ዘርፎችን መለየቱን አድንቀዋል።
ልዩ መልዕክተኛው በኮሪያ ሪፐብሊክ የሚገኝ ትልቁ የኬሚካል ማምረቻ ካምፓኒ ዋና ስራ አስፈጻሚ መሆናቸውም ተገልጿል።