ቀጥታ፡

የህዳሴው ግድብን አራተኛና የመጨረሻ የውሃ ሙሌት መሳካቱ የአባይ ወንዝ  ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከዳር ማድረስ እንደሚያስችል ተገለጸ

ባህር ዳር ፤ መስከረም 2/2016 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት መሳካቱ ኢትዮጵያ  በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አቋም ከዳር ማድረስ እንደሚያስችል ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የህዳሴው ግድብን አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። 
 
ይህን ተከትሎ ኢዜአ ካነጋገራቸው መካከል የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር  አቶ ተስፋሁን አለምነህ፤ ግድቡ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን በመቋቋም ከዚህ ደረጃ መድረሱ ለሀገራችን ታላቅ ድል ነው ብለዋል። 
 
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የአስተሳሰብና  የተግባር አንድነት በማሳየታቸው የተመዘገበ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። 
 
ይህም በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ ስራዎች በአንድነት በመሳተፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለስኬት እንዲበቃ ማስቻሉን ተናግረዋል።
 
አራተኛና የመጨረሻው ሙሌት  በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አቋም  እውን እየሆነ መምጣቱን እንደሚያረጋግጥም አመላክተዋል። 
 
አቶ ተስፋሁን አክለውም የግድቡን ፕሮጀክት በመጠበቅና በመንከባከብ ለታለመለት አገልግሎት ማዋል በቀጣይ ከእኛ የሚጠበቅ ነው ብለዋል። 
 
ግድቡ በደለል እንዳይሞላና ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ከምንጊዜውም በላይ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። 

 
የህዳሴው ግድብን አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቅ መቻላችን በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ታላቅ ድል ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ ናቸው። 
 
ባለፈው ዓመት ሁለት ተርባይኖች ሃይል በማመንጨት ሀገራዊ የሃይል እጥረትን ለማቃለል ጥረት መደረጉን ጠቁመው፤ በቀጣይ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያስፈልገውን ሃይል በማመንጨት ችግሩ እንደሚፈታ ካለው አቅም መረዳት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ለዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ በሚችለው አቅም ሁሉ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል።

  
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ አቶ ግዛት አብዩ በበኩላቸው፤ መንግስት ቃል በገባው መሰረት ግንባታውን በማካሄድ የህዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻ ሙሌት ማሳካቱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል። 
 
የግድቡ በስኬት መቀጠል ሀገራችን በአባይ ወንዝ ላይ የያዘችውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህን ዳር ለማድረስ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት የገባውን ቃል በተግባር ያረጋገጠበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል። 
  
ይህም ሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ተስፋ ሰጪ የፕሮጀክት አፈጻጸም መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም