የሕዳሴው ግድብ የአገርን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ ጫናን ለመቀነስ ያግዛል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ የአገርን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ ጫናን ለመቀነስ ያግዛል-ምሁራን
ሀዋሳ ፤ መስከረም 2/2016 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአገሪቱን የልማት ጉዞ በማፋጠንና የኢኮኖሚ አቅሟን በማሳደግ ጫናን ለመቀነስ ያግዛል ሲሉ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
የሕዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን ተባብረው ከሰሩ የማይሻገሩት ፈተና እንደሌለ ማሳያ መሆኑንም ምሁራኑ ጠቅሰዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሀይድሮሊክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሞልቶት ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።
ይህም በተለይ ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለመቋቋም ከማስቻሉ ባለፈ ኢትዮጵያ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷ እንዲጎለብት ያግዛል ብለዋል።
የግድቡ የውሃ ሙሌት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱ የመተባበር ውጤት መሆኑን ጠቁመው የሕዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ የጀመሩትን መጨረስ እንደሚችሉ የሕዳሴው ግድብ ማሳያ ነው" ብለዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንዲነሱ ማድረጉን አስታውሰው፣ "በአሁኑ ወቅት በትናንሽ ነገሮች የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በመተው አብሮነትን ማጠንከር ይገባል" ሲሉም አክለዋል።
ዶክተር ሞልቶት አክለውም ግድቡ ለቱሪዝም፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለሀገር ገጽታ ግንባታ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያጎለብታል።
ግድቡ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ በግድቡ ዙሪያ የተፋሰስ ልማት ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠልና የአፈር መከላትን መከላከል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዩኒቨርሲቲው የመስኖ ሀብትና ውሀ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተመራማሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቴዎድሮስ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር የገጠሙ ችግሮችን ተቋቁሞ የውሃ ሙሌት ሥራው መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሥራውን ለማስተጓጎል በኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መንገድ ተጽዕኖ ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከዚህ ባለፈ በሀገር ውስጥ የተለያዩ ፈተናዎች እንደነበሩ ያስታወሱት ዶክተር ቴዎድሮስ፣ “ይህን ሁሉ ፈተና በመቋቋም ግድቡ ለዚህ ደረጃ በመድረሱ አስደስቶኛል" ብለዋል።
ዶክተር ቴዎድሮስ እንዳሉት ግድቡን ለመስራት ኢትዮጵያውያን ገንዘብ በማዋጣት፣ ቦንድ በመግዛት፣ በዕውቀትና በተለያዩ መንገዶች ያደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር።
ኢትዮጵያውያን ከተባበርን የሕዳሴ ግድብን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ትላልቅ ልማቶችን ማከናወንና ህዝብንም ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ግድቡ ማሳያ ነው ብለዋል።
የግድቡ አራተኛና የመጨረሻ የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በቀጣይ በግድቡ ዙሪያ በዲፕሎማሲያዊ መስክ ለምታከናውናቸው ሥራዎች ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።