ቀጥታ፡

በመስከረም ወር የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለግብርና ሥራ አዎንታዊ ሚና አለው - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 2/2016 (ኢዜአ)፦ በመስከረም ወር የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት የሚኖረው የአየር ሁኔታ ለግብርና ሥራ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በመስከረም ወር የመጀመሪያዎቹ 10 ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይችላል ብሏል።

በሂደትም የዝናብ ሥርጭቱ በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ እንደሚያተኩርም የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ሁኔታ እየተካሄደ ላለው አጠቃላይ የግብርና ዘርፍ ገንቢ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል። 

የአየር ሁኔታው ቀደም ብለው ለተዘሩ፣ ፍሬ በመያዝ ላይ ለሚገኙና ዘግይተው ለተዘሩ እንዲሁም በተለያየ እድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎችም ሆነ ለቋሚ ተክሎች የተሟላ እድገት የሚያስፈልጋቸውን የውሃ አቅርቦት ከማረጋገጥ አንጻር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብሏል ኢንስቲትዩቱ። 

በአንጻሩ የእርጥበት ሁኔታው ከሰሜንና ከሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች እየቀነሰ እንደሚሄድና በሂደት እንደሚቆም የትንበያ መረጃው እንደሚያመላክት ተገልጿል።

በሌላ በኩል በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙና አልፎ አልፎ ከባድ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችልም ተመላክቷል።

ይህንንም ተከትሎ በትንበያው በተጠቀሱት አካባቢዎች አስቀድሞ ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስትቲትዩቱ አሳስቧል።

በተለይም በአንዳንድ ቦታዎች በከባድ ዝናብ ምክንያት በሚፈጠረው ከመጠን በላይ እርጥበት ውሃ ማሳ ላይ እንዳይተኛ፤ የውሃ መውረጃዎችን መሥራትና ነባር የሆኑ የፍሳሽ መውረጃዎችን የውሃ ፍሰትን ከሚከለክሉ ነገሮች ማጽዳት እንደሚያስፈልግም ገልጿል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም