በአዲስ አበባ  የመሬት አገልግሎትን በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው-የከተማዋ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 2/2016 (ኢዜአ) ፦ በአዲስ አበባ የመሬት አገልግሎትን በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችል የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  የከተማዋ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባሉት ጽህፈት ቤቶቹ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መስጠት ፣ ህጋዊ ሰነድ ላላቸው ይዞታዎች ዋስትናና፣ እዳ የመመዝገብ ስራዎችን ያከናውናል።

በተጨማሪም በወሰን ማስከበር ተግባራት ዘርፍም እንዲሁ የወሰን ችካል፣ የግንባታ ክትትል፣ የለማ መሬትን በምደባ ወይም በጨረታ ማስተላለፍ፣ ካርታ መስጠትና ሌሎችም ይገኙበታል።

ይሁን እንጂ በከተማዋ የሚሰጠው የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች የመልካም አስተዳደር እጦት በስፋት የሚነሳበትና ህገ- ወጥነት የተበራከተበት መሆኑ ይነገራል።

ኢዜአ የመሬት አገልግሎትን በሚመለከት የተገልጋዮች ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያነሳበት መሆኑን ተከትሎ ተከታታይ ዘገባዎችን መስራቱ ይታወቃል።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የመሬት አገልግሎት በሚመለከት ከክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጅነር አሸብር አበራን አነጋግሯል።

በክፍለ ከተማው የፋይል መጥፋትና የሙያተኞች ያልተገባ አገልግሎት አሰጣጥና የስነ-ምግባር መጓደል እንዲሁም በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ህገ- ወጥ ደላሎች በስፋት መኖር ለችግሩ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የመሬት አገልግሎትን ተከትሎ ለሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ አስፈልጓል።

በዚህም አገልግሎቱን ላልተወሰነ ጊዜ በማቋረጥ ፋይል የማጣራትና የመመርመር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም የመሬት አገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት በሚፈለገው ልክ  የሚያዘምኑና የሚያቀላጥፉ በቂ ሙያተኞች አለመኖራቸውም እንዲሁ ሌላኛው መንስኤ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የማሻሻያ ስራው በዋናነት የፋይል ልየታና ማጣራት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ በአጠቃላይ በክፍለ ከተማው ካሉት 51 የፋይል ማስቀመጫ ሳጥኖች ውስጥ (ላተራሎች) 50ዎቹ ተቆጥረው ማለቃቸውን ይናገራሉ።

የፋይል ልየታው ቀደም ሲል የነበረውን የማንዋል አሰራር ሙሉ ለሙሉ በማስቀረት በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ የሚያስችል መሆኑንም እንዲሁ።

አሰራሩ ተገልጋዮች ከፋይል መጥፋትና ከተንዛዛ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ለሚያነሱት ቅሬታ ምላሽ እንደሚሰጥ ታምኖበታልም ብለዋል።

በመሆኑም የተሻለ አገልግሎትን ለመስጠት እየተከናወነ ያለው የማሻሻያ ስራ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፉ እየተቃረበ መሆኑን በመረዳት ተገልጋዮች በትእግስት እንዲጠባበቁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በበኩሉ የነዋሪዎች የቅሬታ መነሻ በማድረግ የከተማዋ የመሬት አገልግሎቶች ለማቀላጠፍና ለማዘመን የሚያስችል የሪፎርም ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጌታቸው እንደገለጹት የከተማዋ የመሬት አገልግሎቶች ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ የማሻሻያ ስራዎችን ለማከናወን የሚያግዝ ሪፎርም እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።

ሪፎርሙ በዋናነት የቴክኖሎጂ አሰራሮችን መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ይህም በዘርፉ ለዘመናት የተከማቸውን ውስብስብ አሰራር እልባት ለመስጠት ያግዛል።

ለአብነትም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ እየተደረገ ያለው ፋይልን የማጥራት ስራ የሪፎርሙ አካል መሆኑንና መሰል ተግባራትንና ሌሎች የማሻሻያ ስራዎችን ወደ ሁሉም ክፈለ ከተሞች የማስፋቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም