የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የዓላማ ጽናት ውጤት ነው---የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የዓላማ ጽናት ውጤት ነው---የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች
ጋምቤላ፤መስከረም 2/2016 (ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አራተኛና የመጨረሻ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የዓላማ ጽናት ውጤት መሆኑን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ መደሰታቸውንም የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት ዓርማ የሆነው የሕዳሴው ግድብ አራተኛና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ የኢትዮጵያውያንን የዓላማ ጽናትና አይበገሬነት ለዓለም ማህበረሰብ የሚያሳይ ነው።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አስቻለው ታዬ እንደገለጹት፣ "የውስጥና የውጪ ተጽኖዎችን በመቋቋም የግድቡ 4ኛ የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቁ እንደ ህዝብ ያለንን ህብረትና ጽናት ያሳያል"ብለዋል።
አቶ አስቻለው እንዳሉት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለግድቡ በአንድነት ቆመው በመረባረባቸው የአይቻልም አስተሳሰብን ከመስበር ባለፈ የተጀመረን ሀገራዊ ፕሮጀክት በራስ አቅም መጨረስ እንደሚቻል ያሳዩበት ነው።
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያዋጣቸው ገንዘብ ሥራ ላይ ውሎ አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቁን ስትሰማ መደሰቷን የገለጸችው ሌላዋ የከተማ ነዋሪ ደግሞ ታዳጊ ህጻን ቤተልሄም ኡጁሉ ናት።
አቶ ፒተር አማን የተባሉ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፣ የግድቡ ግንባታ በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያዋጣው ገንዘብ ዛሬ ለፍሬ በቅቶ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
"የሕዳሴው ግድብ የአንድነታትና የኩራታችን አርማና መገለጫ ነው" ያሉት አቶ ፒተር፣ የግድቡ መገንባት አብሮነትን ከማጠንከር ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው አመልክተዋል።
"የሕዳሴው ግድብ ከውጭም ከውስጥም በርካታ ፈተናዎች ስለነበሩት የውሃ ሙሌት ሥራው እንቅፋት ይገጥመዋል የሚል ስጋት ገብቶኝ ነበር" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ቱት ጋች ናቸው።
በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያዊያን ባሳዩት ህብረትና የዓላማ ጽናት የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት ተጠናቆ በማየታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ለሕዳሴው ግድብ ሲያደርጉት የቆዩትን ተሳትፎ በሌሎች መሰል ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች ላይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።