ቀጥታ፡

የሕዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው -- የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ፤ መስከረም2/2016 (ኢዜአ) ፡- የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ሥራ መጠናቀቅ ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት መረጋገጥ ከሚኖረው ጠቀሜታ ባለፈ የትውልዱ ተስፋ እንዲያብብ ያደርጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ የሕዳሴው ግድብ አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት፤ የግድቡ የውሃ ሙሌት ሥራ በስኬት መጠናቀቅ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ደስታ ፈጥሯል።

በተለይ የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ከቃላት በላይ የሆነ ደስታ እንደፈጠረባቸው ነው ከህፃን ናትናኤል ሙሉአለም ጀምሮ እስከ አዛውንቱ አቶ አለሙ መኮንን የተናገሩት።

ታዳጊ ህፃን ናትናኤል እንደገለጸው፤ ለእሱ ትልቅ ተስፋን ያጎናጸፈው የሕዳሴው ግድብ በቀጣይም ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው። 

"ፍላጎቴም ኢትዮጵያ ከፍ እንድትል ነው" ሲልም ግድቡ ያሳደርበትን ተስፋ ተናግሯል።

ወጣት ከበደ እጅጉ በበኩሉ እንደገለፀው፤ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ አስተዋጾኦው የጎላ እና የወጣቱን ተስፋ ያነቃቃ ፕሮጀክት ነው ብሏል።

"ጫማ ከሚጠርገው እስከ ባለሃብቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በተረባረቡበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጪው የኢትዮጵያ ከፍታ ዕውን መሆኑ አይቀርም "ያለችው ደግሞ ወይዘሪት ሄዋን አለሙ ናት።

አቶ ፌኑስ አብዱልጀባር በበኩላቸው "የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ገጽታዋን በአዲስ ታሪክ የሚገነባ ነው" ብለዋል።

በተለይ ልማትን በማፋጠን ድህነትን ለማስወገድ የተጀመረውን ጉዞ በተሳካ መንገድ ዳር ለማድረስ የግድቡ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ነው የተናገሩት ።

አዛውንቱ አቶ አለሙ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፤ የግደቡ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ትውልዱ የራሱን አዲስ ታሪክ የጻፈበትና ተስፋውን ያነቃቃ ነው ብለዋል።

በተለይ የኢትዮጵያን ዕድገት ለማፋጠንና እና ዜጎችን የኤሌክትሪክ ሐይል ተጠቃሚ ለማድረግ ግድቡ ወሳኝ መሆኑን ነው አቶ አለሙ የተናገሩት።

ነዋሪዎቹ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እስኪገባ ድረስ ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም