በአዲሱ ዓመትም ህግና ሰላምን ለማስጠበቅ በትኩረት እንሰራለን - ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመትም ህግና ሰላምን ለማስጠበቅ በትኩረት እንሰራለን - ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ
ደሴ፤ መስከረም 1/2016(ኢዜአ)፡- በአዲሱ ዓመትም ህግን ለማስከበርና ሰላምን ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰሩ የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ አካላት የዘመን መለወጫ በዓልን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በደሴ ከተማ አክብረዋል፡፡
በዚህ ወቅት ብርጋዴር ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ሰራዊቱ የሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተካሄደው ህግ ማስከበር የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉን ጠቅሰው፤ እንዳለፈው ዘመን ሁሉ በአዲሱ ዓመትም ህግና ሰላምን በማስጠበቅ ህብረተሰቡ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር የዕለት ተዕለት ስራውን መከወን እንዲችል በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡
በዓሉን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ማክበራቸው የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባለፈ ሰራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር ያለውን ቁርኝት የበለጠ ያሳድጋል ሲሉ አመልክተዋል።
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የአንድነትና የእድገት እንዲሆን በቅንጅት መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሰራዊቱ አባል ሌተናል ኮሎኔል ዮናስ አዱኛ በበኩላቸው፤ በአዲሱ ዓመት የህብረተሰቡን ሰላም በማረጋገጥ ልማቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡም አንድነቱን ጠብቆ ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሉዓላዊነት ለማስከበር የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ እያደረገ ባለው ሁለንተናዊ ድጋፍም መደሰታቸውን አመልክተዋል።
በአዲሱ ዓመት በከተማው አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ቅድመ ዝግጅት አድርገናል ያሉት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ አባላት ጋር ተቀናጅቶ ያስጠበቀውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በቅንጅት እንሰራለንም ብለዋል፡፡
በዓሉ የተከበረው ማዕድ በማጋራት፣ በኪነ ጥበብ ትርኢትና በሌሎችም ዝግጅቶች ነው፡፡