ማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የዘመን መለወጫ በዓልን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሚገኙ ሕሙማን ጋር አከበረ - ኢዜአ አማርኛ
ማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የዘመን መለወጫ በዓልን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሚገኙ ሕሙማን ጋር አከበረ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 1/2016 (ኢዜአ) ፦ ማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የዘመን መለወጫ በዓልን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ ሕሙማንና አስታማሚ ቤተሰቦቻቸው ጋር አክብሯል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይም ለህሙማኑ ማዕድ አጋርቷል።
የካንሰር ሶሳይቲው መሥራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ወንዱ በቀለ፤ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሚገኙ ሕሙማንና አስታማሚ ቤተሰቦቻቸው ጋር በማክበራችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
የካንሰር ህመም በጊዜ ከተደረሰበትና ህክምና ከተደረገለት የሚድን በሽታ መሆኑን ጠቅሰው ለጤና ትኩረት በመስጠት የመመርመር ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የጤና ምርመራ በማድረግ ካንሰርንና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞችን መከላከል እንደሚቻል ጠቁመው፤ በአዲስ አመት ሁላችንም ለቅደመ ጤና ምርመራ ትኩረት እንስጥ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአዲስ ዓመት ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ሂደት ማቲዎስ ወንዱ-የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ የድርሻውን እንደሚያበረክትም አረጋግጠዋል።
በውጭም ይሁን በሀገር ቤት የሚኖሩ ግለሰቦችና ተቋማትም ሶሳይቲው ለሚያከናውናቸው ተግባራት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በዛሬው ዕለትም የዘመን መለወጫ በዓልን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኙ ሕሙማንና አስታማሚ ቤተሰቦቻቸው ጋር አክብሯል
የካንሰር ሶሳይቲው እ.አ.አ በ2004 የተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን 1 ሺህ 400 አባላት፣ ከ500 በላይ በጎ ፍቃደኞች እና 30 ሰራተኞች አሉት።