በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አዲስ ዓመትን አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አዲስ ዓመትን አከበሩ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 1/2016 (ኢዜአ) ፦ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አዲስ ዓመትን በኤምባሲዎችና በቆንስላ ጽህፈት ቤቶች አክብረዋል።
አዲስ ዓመት (ዘመን መለወጫ) በዓል ከተከበሩባቸው አገራት መካከል አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጅቡቲ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ስዊዘርላንድ፣ ጃፓንና ደቡብ ሱዳን ይጠቀሳሉ።
በዓሉን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለያዩ መርሃ ግብሮች በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች አክብረውታል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ አምባሳደሮች ለመላ ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተለይም ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያ ለጀመረቻቸው ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ስኬት እያደረጉ ያለውን ድጋፍ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅርና የአብሮነት እንዲሆንም የመልካም ምኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።