የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ምክንያቶችን በአግባቡ በመረዳት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ ውጤት እያመጣ ነው- ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ምክንያቶችን በአግባቡ በመረዳት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ ውጤት እያመጣ ነው- ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 1/2016 (ኢዜአ) ፦ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ምክንያቶችን በአግባቡ በመረዳት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ ውጤት እያመጣ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
በአዲስ አበባ በአዲስ ዓመት ከዋዜማው ጀምሮ እስካሁን ምንም አይነት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አለመከሰቱንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ፤ በአዲስ ዓመት የበዓል አከባበር ላይ እሳትና ድንገተኛ አደጋ እንዳይከሰት ኮሚሽኑ ቀደም ብሎ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በተለየም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች በስፋት መከናወናቸውን ነው የተናገሩት።
አደጋ እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከልና ካጋጠመም ፈጣን ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲከናወን መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በመሆኑም ሕብረተሰቡ ከኮሚሽኑ የተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበሩ ከዋዜማው ጀምሮ እስካሁን ምንም አይነት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አለመከሰቱን ገልጸዋል።
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ምክንያቶችን በመረዳት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
በዓሉ የሚቀጥል በመሆኑ ሕብረተሰቡ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በተለመደው መልኩ መተግበሩን እንዲቀጥልና አደጋ ካጋጠመም ለኮሚሽኑ በፍጥነት ሊያሳውቅ ይገባል ብለዋል።
የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ካጋጠመ በነጻ የስልክ መስመር 939፣ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 0111555300 ወይም በ0111568601 በመደወል ማሳወቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል።