ቀጥታ፡

አዲሱ ዓመት የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ጠንክረን የምንሰራበት ሊሆን ይገባል--ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ

ጅግጅጋ (ኢዜአ)ጳጉሜን 6/2015--አዲሱ ዓመት የህዝባችን መገለጫ የሆነውን የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ጠንክረን የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ ገለጹ።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የ2016 አዲስ ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። 

በእዚሁ ጊዜ አቶ ሙስጠፌ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው ዓመት በአብሮነት እና በመቻቻል እሴቶች ችግሮችን በመሻገር የክልሉን ህዝብ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መመለስ ተችሏል። 

"በርካታ የልማት ሥራዎችን በመስራት ህዝባችንን ተጠቃሚ ማድረግ የቻልንበት ዓመት ነበር" ሲሉም አቶ ሙስጠፌ ገልጸዋል። 

የሀገራችን ህዝቦች የጋራ አሻራ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድባችን አራተኛ የውሃ ሙሌት በስኬት ያጠናቀቅንበት፣ የልማት ፕሮጀክቶች የተመረቁበት እና ግጭቶችን በሰላም የፈታንበት ዓመት ነበር ሲሉም አመልክተዋል። 

አቶ ሙስጠፌ እንዳሉት በክልሉ የህዝቡን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር ዜጎች በሰላምና በመቻቻል አብሮ በመኖር በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ይበልጥ ማረጋገጥ ተችሏል።

አዲሱ ዓመት የህዝባችን መገለጫ የሆነውን የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶች በማጠናከር የብልጽግና ጉዞውን እውን ለማድረግ ጠንክረን የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልካም ምኞት መግለጫቸው በክልሉ በ2015 በግብርናና በአርብቶ አደር ልማት፣ በጤና፣ በውሃ፣ በመንገድ፣ በገቢ እንዲሁም በሌሎች በርካታ የልማት ሥራዎች ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅስዋል።

"የክልሉን ገቢ በማሳደግ በኩልም በዓመቱ ከዕቅድ በላይ ገቢ በመሰብሰብ አመርቂ ውጤት የተመዘገቡበት ዓመት ነበር" ሲሉም አመልክተዋል። 

በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ ዓመት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች የሚሳኩበት፣ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች የሚጠናከሩበት እንዲሁም የሰላም፣ የጤናና፣ የብልፅግና ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። 

--

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም