ቀጥታ፡

አዲሱ አመት አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበትና አዳዲስ ውጥኖችን ለማሳካት የምንተጋበት እንዲሆን እመኛለሁ-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ጳጉሜን 6/2015(ኢዜአ)፦ አዲሱ አመት አዲስ ተስፋ የምንሰንቅበት፣ አዳዲስ ውጥኖችን ለማሳካት የምንተጋበት፣ የጎደለው ሁሉ እንደ ህዳሴው ግድብ የሚሞላበት፣ የማይቻል የሚመስለን ሁሉ እንደ ግድባችን ተችሎ ሃሴት የምናደርግበት የስኬት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለ2016 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “2015 ዓ.ም ከመላው የከተማችን ነዋሪ ጋር በጋራ እያቀድንና እየተወያየን ለጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠን ከተማችንን ከፍ ለማድረግ በትጋት ሰርተን ስኬት የተጎናፀፍንበት እና ፈተናዎችን በጸናው ሕብረታችን ያለፍንበት ዓመት ነበር” ብለዋል::

የረዳንና ያሳካልን ፈጣሪ ይመስገን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

“በስራዎቻችን ሁሉ ከጎናችን ለተሰለፋችሁ የከተማችን ነዋሪዎች፣ አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ልበ-ቀና ባለሀብቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሁሉ አብረን ላሳካናቸው ስኬቶች ምስጋናችን ይድረሳችሁ” ብለዋል።

“ለመቀበል በተዘጋጀነው 2016 ዓመት አዲስ ተስፋ የምንሰንቀበት፣ አዳዲስ ውጥኖችን ለማሳካት የምንተጋበት፣ የጎደለው ሁሉ እንደ ህዳሴው ግድብ የሚሞላበት፣ የማይቻል የሚመስለን ሁሉ እንደ ግድባችን ተችሎ ሃሴት የምናደርግበት እንዲሁም ሰላማችን እንደ ህዳሴው ግድብ ሞልቶ የሚፈስበት የለውጥ እና የስኬት ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም