ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ ለያዘችው የልማትና የእድገት ጉዞ የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ማዋሏ አስፈላጊና ተገቢ ነው-የውሀ ዘርፍ ምሁራን

አርባ ምንጭ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ ለያዘችው የልማትና የእድገት ጉዞ የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ማዋሏ አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሀ ዘርፍ ምሁራን ገለጹ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛውና የመጨረሻው ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢዜአ በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሀ ዘርፍ ምሁራንን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሯል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛውና የመጨረሻው ዙር የውሀ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ “የመንግስትና የህዝቡ ቁርጠኝነት ውጤት ነው” ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዉሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ቦጋለ ገብረማሪያም እንደገለጹት ከዚህ ቀደም አባቶች አብሮነታቸውን በአድዋ ድል ላይ እንዳስመዘገቡ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም አብሮነቱን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በመድገም የራሱን ታሪክ እየፃፈ ይገኛል።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያን በጋራ አሻራቸውን ማኖራቸውን ጠቅሰዋል።

“የግድቡ ግንባታ ህዝቡን ከዳር ዳር ያነቃነቀ አብሮነቱንና አንድነቱን ይበልጥ ያጠናከረ ነው” ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በርካታ የውስጥና የዉጭ ጫናዎችን ተቋቁማ አራተኛውና የመጨረሻውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋ የህዝቡና የመንግስት ቁርጠኝነትና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጠንካራ ሥራ መሰራቱን የሚያመላክት ነው” ሲሉ ዶክተር ቦጋለ ጠቅሰዋል።

ዶክተር ቦጋለ አክለውም “ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚዋ በጣም እያደገ በመምጣቱ የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ማዋል ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

የሀገር ውስጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገትን ተከትሎ የኢትዮጵያ የሃይል ፊላጎት በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

እንደሀገር እየተካሄደ ያለው ሁለንተናዊ ዕድገት የማረጋገጥ ሂደትን በአግባቡ ለማስኬሄድ በሀይል ፍላጎት ላይ መስራቱ ተገቢ መሆኑን አንስተው ለዚህ ደግሞ የህዳሴው ግድብ ምላሽ ይዞ የመጣ መሆኑን አመልክተዋል።

የሀይል ፍላጎት ከልማት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸው ካለን የልማት ፍላጎትና ድህነትን የማሸነፍ ትግል አንጻር ይህ ብቻ በቂ ነው ብለን የምንተወው ሳይሆን ለሌላ ግድብ ስራም መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛውና የመጨረሻውን ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ማጠናቀቋ መንግስትና ህዝብ የግድቡን ግንባታ ዳር ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የውሃ ዘርፍ ተመራማሪና መምህር ዶክተር ደመላሽ ወንድማገኘው ናቸው።

ሀገር ለማልማት የተሰራው አስደናቂ ስራ ልዩነትን ወደ ዳር ትቶ ለአንድ ዓላማ በአንድ ላይ እንዲሰለፉ ማድረግ የቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀብትን ለመጠቀም ህዝብና መንግስት በጋራ ያደረጉት ርብርብ ለሌሎች የአፍርካ ሀገራት ጭምር ያስተማረና መነሳሳትን የፈጠረ እንዲሁም የነበረንን አብሮነት ይበልጥ እንድናጠናክር ያስቻለ ነው ብለዋል።

የወንዙ ፍሰት ክረምት ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የውሃው ሙሌት ደግሞ በክረምት ወቅት እንዲሆን እንደሀገር ታስቦ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ላይ የውሃው መጠን እንዳይቀንስና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ለመከተል የተደረገ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል አብሮ መልማትን በመርህ ላይ ቆማ የምትደግፍ ሀገር መሆኗን በተግባር ያሳየችበት ነው ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛውና የመጨረሻው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ ቀሪ የግንባታ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ከማነሳሳትም በላይ በቀጣይ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ለህዝቡ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉ ዶክተር ደመላሽ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም