በአዲሱ ዓመት የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል---ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት ይሰራል---ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ (ኢዜአ) ጰጉሜን 6/2015--በአዲሱ ዓመት የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በእዚሁ ጊዜ እንዳሉት በተጠናቀቀው የ2015 ዓ.ም በክልሉ የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች አጋጥሞ የነበረው የፀጥታ ችግር በህብረተሰቡና በፀጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት በአሁኑ በክልሉ ሰላም ለማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።
ሰላሙን ዘላቂ በማድረግ በአዲሱ ዓመት የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አቶ ኡሞድ ገልጸዋል።
በአዲሱ ዓመት በክልሉ ሠላምንና ልማትን ለማስቀጠል እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች ጎን ለጎን ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራም አቶ ኡሞድ አስታውቀዋል።
ክፍተቶችን አርሞ ስኬቶቹን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚከናወኑ ስራዎች የሁሉም ዜጋ የጋራ ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ርዕሰ መስተዳደሩ አመልክተዋል።
እንደ አቶ ኡሞድ ገለጻ በአዲሱ ዓመት በ2015 ዓ.ም የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን ማስቀጠል፣ የተስተዋሉ ውስንነቶችን ማረምና ፈተናዎችን በአብሮነት ማለፍ ይገባል።
በክልሉ በፀጥታ ምክንያት ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በቀጣይ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም የክልሉ መንግስት ትኩረት መሆኑን አመልክተዋል።
አዲሱ ዓመት የሰላምና የልማት ሥራዎች የሚጠናከሩበት፣ ግጭትና አለመግባባቶች የሚወገዱበትና ችግሮች ሁሉ የሚፈቱበት እንዲሆን አቶ ኡሞድ መልካም ምኞታቸውንም ገልፀዋል።
የክልሉ ህዝብ ሰላምን በዘላቂነት በማጠናከር የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እውን እንዲሆኑ ተሳትፎውን እንዲያጠናክርም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።
በዓሉን በተለያየ ምክንያት የተቸገሩትን ወገኖች በመርዳት እና በመንከባከብ አብሮ ማሳለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲሱ ዓመት ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የመረጋጋት፣ የፍቅር፣ የደስታ እና የአንድነት እንዲሆንም ተመኝተዋል።