የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ለአዲሱ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ለአዲሱ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 6/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለሀገሪቱ ፖሊስ ሠራዊት እንዲሁም ለሌሎች የፀጥታና ደኅንነት አካላት እንኳን ለ2016 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም "ባሳለፍነው ዓመት ሕዝባችንን ከጎናችን አሰልፈን የገጠሙንን የፀጥታ ችግሮች መመከት እንደቻልን ሁሉ በአዲሱ ዓመትም ከሕዝባችን ጋር ሆነን አንፀባራቂ ውጤት በማስመዝገብ የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋና የተቋማችንን ራዕይ የምናረጋግጥበት ዘመን እንደሚሆን ሙሉ እምነት አለኝ" ሲሉ ገልጸዋል።
የወንጀል መከላከልና የወንጀል ምርመራ አፈፃፀም አቅም ብቃት ባለው የሰው ኃይል፣ በተለያዩ ዘመናዊ ትጥቆችና ቴክኖሎጂዎች በማጠናከር የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት የሚረጋገጥበት እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል።
ኮሚሽነሩ “በሀገራችን የፖሊስ አገልግሎት የመጀመሪያ የሆነው የዜጎች ተሳትፎ ማዕከል (Citizen Engagement Center) መተግበሪያ አጠናቀን ለሕዝብ የምናስተዋውቅበት እና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ የምናሳድግበት ዓመት እንዲሆን በቁርጠኝነት እንሰራለን” ሲሉም ጠቅሰዋል።
አዲሱ ዓመት የፖሊስ ሠራዊቱ ኑሮ በሁለንተናዊ መልኩ ለማሻሻል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት ዓመት ይሆናል ማለታቸውንም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
በመጨረሻም መላው የሀገሩቱ ፖሊስ ሠራዊት ሕዝቡን በማሳተፍ እና ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር ተቀናጅቶ እያከናወነ ያለውን ፀጥታን የማስከበር ተግባር ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።