የኢትዮጵያዊያን መልካም እሴት መገለጫ የሆነውን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል- ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያዊያን መልካም እሴት መገለጫ የሆነውን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል- ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያዊያን መልካም እሴት መገለጫ የሆነውን አብሮነት በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር "በሕብር የተሰራች አገር" በሚል እየተከበረ ያለውን የአብሮነት ቀን በማስመልከት ከተጠሪ ተቋማትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቀኑን የተመለከተ የእግር ጉዞ አካሄዷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ ጥንት አባቶቻችንን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ጸንታ እንድትቆም ካስቻሉባቸው መንገዶች አንዱ ለአንድ ዓላማ በአብሮነት መቆማቸው ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካስቻሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን መካከል አብሮነት ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ወቅቶች የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በአብሮነት መሻገራቸውን አመልክተዋል።
የአብሮነት ቀንን ስናከበር መልካም ባህላዊ እሴቶቻችንን በማስጠበቅና ቂምና ቁርሾን በይቅርታ በመፍታት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው በበኩላቸው ስፖርት በባህሪው ተባብሮ አብሮ መስራትን የሚጠይቅ ዘርፍ መሆኑን ገልጸው ከዚህ አኳም አብሮነት በስፖርቱ ልዩ ቦታ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ሰላም የሁሉ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው ይህንን እውን ለማድረግ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴዓትር የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኩሪ አየለ በበኩላቸው አብሮነት ኢትዮጵያውያን ለረጅም ዘመናት መቆየታቸውን ገልጸው ይህን መልካም እሴት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።