አብሮነት በሁሉም የስራ መስክ የድል መሰረት ነው - በ19ኛው የቡዳፔስት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ አትሌቶች - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነት በሁሉም የስራ መስክ የድል መሰረት ነው - በ19ኛው የቡዳፔስት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ አትሌቶች

አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፦ አብሮነት በሁሉም የስራ መስክ የድል መሰረት ነው ሲሉ በ19ኛው የቡዳፔስት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊ አትሌቶች ተናገሩ።
ዛሬ ጳጉሜን 6 የአብሮነት ቀን "በሕብር የተሰራች ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል።
ኢትዮጵያውያን በአብሮነት እሴት ድልና ተግዳሮቶችን በጋራ በማለፍ የሀገር ሕልውናን ማስጠበቅ ችለዋል።
በየትውልዱ የነበሩ የአብሮነት እሴቶች ለሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስነ-ልቦናዊ ከፍታ መሰረት ሆነው፣ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ በድል ታጅበው እንዲዘልቁ አስችሏል።
ከሀገር ክብርና ገጽታ አኳያ የአብሮነት ትሩፋት መካከል አንዱ የአትሌቲክስ ዘርፍ ሲሆን ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በዓለም መድረክ ላይ የታየው ድል በዚህ በኩል ተጠቃሽ ነው፡፡
የሀገርን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የሚወዳደሩ አትሌቶች 'አረንጓዴው ጎርፍ' የተሰኘ ስያሜ እስኪሰጣችው ድረስ ለሀገራቸው ክብር ተባብረዋል፣ በተሰለፉበት ውድድርም አኩሪ ድል አስመዝግበዋል።
በቅርቡ በሀንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳታፊዎችም በቡድን በመስራት የሀገር ስምና ክብር ከፍ እንዲል ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡
የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል ውድድር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት እና በ19ኛው ቡዳፔስት ሻምፒዮና ላይ በሶስት ሺህ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ለሜቻ ግርማ፣ ለሀገር መስዋዕትነት መክፈል ኩራት እንደሆነ ይገልጻል።
በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና በሴቶች ማራቶን ውድድር በቡድን ስራ ትልቅ ሚና የነበራት አትሌት ፀሐይ ገመቹ በበኩሏ፣ ለሀገርና ህዝብ በማሰብ እስከመስዋዕትነት እንደምትሮጥ ትገልጻለች።
በሻምፒዮናው በወንዶች ማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ልዑል ገብረስላሴም፣ የሀገር ድል በመናፈቅ በማንኛውም ውድድር ላይ ዋጋ መክፈል እንደሚያስፈልግ ይናገራል።
በሴቶች ማራቶን ውድድር በኦሬጎኑ 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን የወርቅ እንዲሁም በ19ኛው የቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ጎይቲቶም ገብረሥላሴም ይህን ሃሳብ ትጋራለች።
በውድድሩ ኢትዮጵያውያን በአብሮነት በመስራት ከወርቅ እስከ ነሐስ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ራስን እስከመሳት የሚያስችል ብርቱ ትንቅንቅ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
በቡዳፔስቱ ውድድር በአየር ጸባዩ ሁኔታ ክብደት የተጠበቀው ውጤት ባይመጣም በአብሮነት እሴት አኩሪ ገድልና ድል ለማስመዝገብ በቡድን እንደሰሩ ተናግረዋል።
በውድድሩ ሁሉንም ሜዳሊያዎች ለማምጣት የተደረገው ጥረት ባይሳካም በቀጣይ የአብሮነት ስራቸውን በማጠናከር ለሀገር አኩሪ ድል ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።