ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጣናው እና የተፋሰሱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ፕሮጀክት ነው- አምባሳደር መለስ ዓለም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ ግድቡ ለአካባቢያዊ ውህደት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሆነው እንደ አንድ በአንጡራ ሀብታቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው እየገነቡት የሚገኝ የኃይል ማመንጫ መሆኑንም ተናግረዋል።

ግድቡ የትውልድን የዘመናት የልማት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ የግድቡ አራተኛና የመጨረሻ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቅም ለኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት ገጸበረከት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት ብዙ ተፅዕኖ ማስተናገዷን በማንሳት፤ በመርህ፣ በቁርጠኝነት እና በጥረቷ ፈተናዎችን ማለፍ ችላለች ያሉት፡፡

ግድቡ በኢትዮጵያውያን የውስጥ አቅም በሉዓላዊ ግዛታቸው ውስጥ የሚገነባ ቢሆንም ጥቅሙ ከሀገር ያለፈ ነው ብለዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኃይል ዘርፍ የጀመረችውን ትስስርና የኢኮኖሚያዊ ውህደት ጉዞ በእጅጉ የሚያጠናክር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የታችኛው የተፋሰስ አገራት የሚገኙ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳያጋጥማቸው እንዲሁም በቂ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ በማድረግም ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ግድቡ የቀጣናውንና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ግድቡ የትብብር እንጂ የግጭት ምንጭ መሆን የለበትም ብለዋል፡፡

አራተኛውና የመጨረሻው ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነው የፖሊሲ ነጻነታችንን መሰረት በማድረግና የኤሌክትሪክ ኃይል ያላገኙ 65 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን የሃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን አንዳንድ አካላት ጉዳዩን በተቃራኒው መውሰዳቸው የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ለሚደረግ ዘመቻ ምላሽና የህዝብ ግንኙነት ስራ ውስጥ መግባት እንደማይፈልግም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የተፈራረመችው ስምምነት እንደሌለ በማንሳት፤ ከዚህ አኳያ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙና ለአንድ ወገን ባደሉ ስምምነቶች ከልማት አትታቀብም ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን የግድቡን ግንባታ እንዳገባደዱት ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ከኢትዮጵያ አልፎ የቀጣናው ብርሃን እንዲሆን ያደርጋሉም ነው ያሉት።

ከታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ጋር ከህዳሴ ግድብ ያለፈ ግንኙነት አለን ያሉት አምባሳደር መለስ ዓለም፤ ኢትዮጵያ በልማት ትብብሮች፣ በህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ጉዳዮች በሚመለከት በትብብረ መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም