የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር የህዝብን አንድነት ማጽናት ይገባል--አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር የህዝብን አንድነት ማጽናት ይገባል--አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም
ሐረር (ኢዜአ) ዻጉሜ 6/2015---የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር የህዝብን አንድነት ማጽናት እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሱልጣን አብዱሰላም ገለጹ።
በክልሉ ጳጉሜን-6 የአብሮነት ቀን “በህብር የተሰራች አገር” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ የታደሙት የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያውያን ደስታና ችግሮችን በአብሮነት የምናሳልፍ ህዝቦች ነን ብለዋል።
በታሪክ ከመቆራኘት ባለፈ የጋራ እሴቶች፣ ባህል እና አኗኗር ያለን ህዝቦች መሆናቸንንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያውያን በአብሮነት ተባብረን ከተነሳን ያቀድነውን ማሳካት እንደምንችል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ማሳያ መሆኑንም አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።
የህዝቦቿን ሰላምና አብሮነት ለመሸርሸር የሚጥሩ አካላት ቢኖሩም መቼም እንደማይሳካላቸው ገልጸው፣ "ህዝቡ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ የሆነውን የአብሮነት ባህል ማጠናከር አለበት" ብለዋል።
የአብሮነት ቀን ስናከብር ለአዲሱ ዓመት በግላችን፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰቡ እና በሥራችን ያቀድነውን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆናችንን በማረጋገጥ ጭምር መሆን እንዳለበትም አቶ ሱልጣን አስገንዝበዋል።
የሐረሪ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዓሉ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የዳበረውን የአብሮነት እሴት ለማስቀጠልና ለትውልድ ለማስተላለፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ለአብሮነት ትኩረት መሰጠቱ እርስ በርስ ለመተባበር፣ ለመረዳዳት እና አንድነትን ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
አብሮነትን ማጠናከርና እሴቱንም በትውልዱ ውስጥ ማስረጽ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ይረዳል ያሉት ደግሞ ከመድረኩ ተሳታፊዎቹ መካከል ወይዘሮ ፈሪሃ መሀመድ ናቸው።
የአብሮነት ቀን በሠላምና በፍቅር የተሳሰረ ጠንካራ ማህበረሰብ ለመፈጠር ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑን በቀጣይም ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የአገር ሽማግሌው አቶ ቶፊቅ ዩሱፍ በበኩላቸው ሐረር ለዘመናት ህዝቦቿ በአብሮነትና በእንድነት የኖሩና በአለም አቀፍ እውቅና የተቸራት ከተማ መሆኗን አስታውሰዋል።
የእብሮነት ቀን ትኩረት ተሰጥቶት እንደ ሀገር መከበሩ ሁሉም አንድነቱን እንዲያጠናክር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።