ቀጥታ፡

በአብሮነትና በአንድነት ተባብረን ከሰራን የማንሻገረው ፈተናና የማናሳካው ድል አይኖርም - ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ቴንኩዌይ ጆክ

ጋምቤላ ፤ ጳጉሜን 6/2015 (ኢዜአ) ፦ በአብሮነትና በአንድነት ተባብረን ከሰራን የማንሻገረው ፈተናና የማናሳካው ድል አይኖርም ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ገለጹ።

ጳጉሜን 6 የአብሮነት ቀን በህብር የተሰራች አገር በሚል መሪ ቃል በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት በአብሮነትና በአንድነት ተባብረን ከሰራን የማንሻገረው ፈተናና የማናሳካው ድል አይኖርም ብለዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሜጋ ፕሮጀክት ያስመዘገብነው ስኬት ለዚህ አብይ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።


 

የክልሉ ህዝቦች በአዲሱ ዓመት አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ለክልሉ ሰላምና ልማት መረጋገጥ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአዲሱ ዓመትም የህዝቡን ወንድማማችነትና እህትማማችነት የሚያጠናክሩ እሴቶቻችን ላይ በማተኮር ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት እያስቀመጥን መሄድም ይኖርብናል ብለዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኡቦንግ ኡቻላ በበኩላቸው አብሮነትና አንድነት ለሀገር ሰላምና እድገት ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአብሮነትና በአንድነት የሰው ልጆችን ማህበራዊ መስተጋብርን በማጎልበት አወንታዊ ሚና መጫወት እንደሚገባ ጠቁመው የአበሮነት ቀን በዚህ መልኩ መከበሩ የህዝቦችን ማህበራዊ መስተጋብር ያጠናክራል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ለአቅመ ደካሞችና ለአረጋውያን ለአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል መዋያ የሚሆን ድጋፍ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም