በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አደአ፤ ጳጉሜን 06/2015 (ኢዜአ) ፦በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ ገለፁ።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ ጎዲኖ ጂቱ ቀበሌ በ20 ሚሊዮን ብር የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀምሯል።
አቶ አብዱልሃኪም ሙሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።
በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ11 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በባለሀብቶች፣ ባለድርሻ አካላትና በክልሉ ህዝብ ተሳትፎ ተገንብተው በመማር ማስተማር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚህም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በዛሬው ዕለትም በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳኣ ወረዳ ጎዲኖ ጂቱ ቀበሌ በ20 ሚሊዮን ብር በየኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ግንባታው የተጀመረው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሚገነባው ትምህርት ቤት ደረጃውን የጠበቀ፣ ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑንም አቶ አብዱልሃኪም ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ ርብርብ እየተደረገ ነው።
ከ11 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ከ23 ሺህ በላይ መምህራን በቅድም መደበኛ ትምህርት ቤቶች እያስተማሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ከ4 ሺህ 700 በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በክልሉ በህዝቡና በባለሃብቶች ተሳትፎ በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ 3 ሺ 410 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በምስራቅ ሸዋ ዞን ባለፉት ሶስት ዓመታት 290 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃቱን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ አባቡ ዋቆ ተናግረዋል።
በዞኑ ባለሃብቶችና በህብረተሰቡ ግንባታቸው ከተጀመረው አዳዲስ 240 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 151 የሚሆኑት ግንባታቸው ተጠናቆ ለ2016 ዓ.ም የመማር ማስተማር ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጄስቲክ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ በበኩላቸው ድርጅቱ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ በትምህርት ቤቶችና በአረጋዊያን ቤት ግንባታ እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሰው በአደኣ ወረዳ ጎዲኖ ጂቱ የተጀመረውም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።